በዶሮ ፣ በበግ እርባታና በዓሳ ሀብት ልማት መስክ የተሰማሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ።

Spread the love

ሀገራዊዉ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእያንዳንዱ ቤተሰብ ብልጽግና ማረጋገጫ መሠረት ተደርጎ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ኢኒሼቲቩ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ሀገራዊ ዕድገትን እውን ለማድረግ መሠረት የጣለ ነዉ።

በካፋ ዞን በጎባ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ በማህበር የተደራጁ ሴቶች፣ ወጣቶችና አርሶ አደሮች በዶሮ ፣ በበግ እርባታና በዓሳ ሀብት ልማት መስክ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው በእንቁላል ዶሮ ፣ በበግ እርባታ፣ በዓሳ ሀብት ልማት እየተከወኑ ያሉ ተግባራትን ተስፋ ሰጪ መሆኑንና በኩታ ገጠም የእንቁላል ዶሮ እርባታ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ችለናል ሲሉም ወጣት አጥናፉ ኬማቶ እና ወ/ሮ አየለች ተካ ይገልጻሉ፡፡

15 ሆነው በማህበር ተደራጅተው LLRP በሚባል መንግሥታዊ ባልሆነ ፕሮጀክት ለእያንዳንዳቸው በተመቻቸላቸው የገንዘብ ድጋፍ

በ20 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እርባታ ስራ የጀመሩትን ስራ በአሁኑ ወቅት የዶሮዎችን ቁጥር በማሳደግ የእንቁላል ምርት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ በማቅራብ ውጤታማ መሆን መቻላቸውንና ትኩረት ሰጥተው ከሰሩት ትርፋማ መሆንና መለወጥ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው በወረዳው ዲሺ ገጠር ቀበሌ በLLRP ፕሮጀክት ድጋፍ በቦንጋ በግ ዝርያ ማሻሻያ ተሰማርተው በግ በማርባት ላይ የሚገኙ አቶ አክሊሉ አለሙ እና አካሉ አባቶ የቦንጋ በግ ዝርያ ከቀድሞው በእድገትና በውጤት የተሻለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህም የተጀመረው ኩታ ገጠም የበግ እርባታ ወደሌሎች ቀበሌዎች እንዲሰፋ አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ በማድረግ የበግ እርባታ በስፋት ለማካሄድ መዘጋጀታቸውንና የሚደረገውን ድጋፍ ተጠቅመው ስራውን በማጠናከር ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

በዲሺ ገጠር ቀበሌ በዓሳ ሀብት ልማት ላይ የተሰማራው አርሶ አደር መላኩ መኩሪያ ወደ ስራ ከገባ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም ዓሳን ማምረት ለራሳቸው እየተጠቀሙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አንድ ምርት የሚሰጥ የዓሳ ጋንዳ እንዳላቸውና ሁለት ተጨማሪ ጋንዳዎችን አዘጋጅተው ለማስፋት ዝግጅት ላይ መሆናቸውንና ስራውን ባግባቡ በመስራት ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በካፋ ዞን የጎባ ወረዳ ምክትል አስተዳደርና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አቦ እንደገለጹት የሌማት ትሩፋት ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሠጥቶ ሴቶች ፣ ወጣቶችና አርሶ አደሩ በየአካባቢያቸው ተደራጅተው በመስራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪና አበረታች በመሆኑ በወረዳው የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

በኡያ ቀበሌ እና ዲሺ ምንጃ መንደር በፕሮጀክት በማስደገፍ ከ50 የሚበልጡ የዶሮ መንደር በመፍጠር በእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ላይ ሴቶችና ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ በተደረገው ጥረት ወደ ሥራ ገብተው ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ በእንቁላል ምርት ገበያን በማረጋጋት ኑሮ ውድነቱን መቀነስ ከፍተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በእንሰሳት ሀብት ልማት በበግ እርባታ ከቦንጋ ግብርና ምርምር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና በዚህም ከቦንጋ ምርጥ የበግ ዝርያ ግዢ በመፈጸም በዲሺ ገጠር ቀበሌ እና በአንገላ ስርጭት መደረጉን ያነሱት አቶ አለማየሁ ስራው በአርሶ አደሩ ዘንድ ጥሩ መነቃቃት ፈጥሯል ለውጥም መጥቷል ብለዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *