የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከልና የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ

Spread the love

‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከዞን ጤና መምሪያ ሀላፊዎች ጋር በወቅታዊ የማርበርግ ቫይረስ ስርጭት እና ቅድመ መከላከል ስራዎች አፈፃፀም ላይ በበይነ መረብ ውይይት አድርጓል።

‎የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንደገለጹት የማርበርግ ቫይረስ ስርጭትን በመግታት የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።

‎ለህብረተሰቡ የማርበርግ ቫይረስ የሚተላለፍበት እና መከላከል በሚቻልበት መንገዶች ላይ ግንዛቤ ለመስጠት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የማህበረሰብ ንቅናቄ መድረኮች አየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

‎ቫይረሱ በሰው ልጅ ጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር የወቅቱ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ የገለጹት ሀላፊው እስካሁን በክልላችን በሽታው ባይገኝም ከሁሉም በላይ የበሽታ ቅኝትና አሰሳው እንዲሁም የጤና ተቋማትን ዝግጁ የማድረግ ተግባር እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎አቶ ኢብራሂም አክለው እንደገለጹት ማርበርግና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል በንቅናቄ በሚሰራበት ወቅት በመደበኛ የጤና አገልግሎት አቅርቦት በተለይም የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ስራዎች መዘናጋት እንዳይፈጠር ጎን ለጎን ሊሰራ እንደሚገባና የ2018 ዓ.ም የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን ዕድሳትና አዲስ አባል የምዝገባ ተግባር በፍጥነት መሻሻል ያለበትና ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

‎የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨመሰ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የማርበርግ ቫይረስ በአጎራባች ደቡብ ኢትዮጵያ አጎራባች ዞኖች ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የቅድመ አሰሳ እና የግንዛቤ ስራዎች እየተሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

‎የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር መላው ህብረተሰቡን አነቃንቆ ከመስራት አንጻር በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

‎የክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ኘሮግራሞች እና ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ በበኩላቸው ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ላይ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ራሱን እንዲከላከል የማህበረሰብ ንቅናቄ መድረኮች እየፈጠሩ እና የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን መረጃን ለማድረስ እየተጠበሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

‎የማርበርግ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከጤና ኬላዎች ጀምሮ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ይገኛሉ ያሉት አቶ ሀይሌ ማርበርግን ጨምሮ ሌሎች በጤና ተቋማት የሚሰሩ የጤና ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

‎የጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎቶች እና የቢሮ ም/ሀላፊ አቶ ምትኩ ታመነ እንደገለጹት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ነባር አባላት እድሳት እና አዲስ አባላት የማፍራት ስራ እየተሰራ ቢሆንም ሁሉን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም ተጠናናክሮ መሰራት አለበት ብለዋል።

‎የማርበርግ ቫይረስ መከላከል እና ለሌሎች የህክምና አገልግሎቶች የሚውሉ መድሀኒቶችና ግብዓቶችን በማቅረብ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የሁሉም ዞን ጤና መምርያ ኃላፊዎች የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከላከልና ዝግጁነት እንዲሁም የማዕጤመ አፈፃፀም ሪፖርት በማቅረብ ተገምግሞ ግብረመልስ መሠጠቱን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *