
በ2016 ዓ.ም በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ የሚቀመጡ ተማሪዎች ምዝገባ ከየካቲት 3 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል።
አገልግሎቱ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የምዝገባ ሂደትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ዘንድሮ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ገልጸዋል።
ከዝግጅቱ መካከልም የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን መመዝገብ የሚያስችል ስራ ማከናወን አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።
የካቲት 3 የተጀመረው ምዝገባ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ምዝገባ የጀመሩ አካባቢዎች መኖራቸውን በማብራራት በቀጣይም ምዝገባ ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች ምዝገባውን እንደሚያካሄዱ ገልፀዋል።
ፈተናው ላይ ለመቀመጥ በመደበኛ፣ በማታ፣ በርቀት እና በግል በሀገር አቀፍ ደረጃ መመዝገብ ከሚያስችሉ መስፈርቶች መካከል ዋነኛው የትምህርት ማስረጃ መሆኑን ተናግረዋል።
በመደበኛ እና በማታ ትምህርት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባ በትምህርት ቤቶች እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
የግል፣ የርቀት እና በበይነ መረብ ተምረው የሚፈተኑ ተማሪዎች ምዝገባ በክፍለ ከተማ፣ በልዩ ወረዳ እና በወረዳ የትምህርት ፅህፈት ቤቶች እንደሚካሄድ አክለዋል።
ከአገልግሎት ባገኘነው መረጃ በ2016 በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ከ870 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
