በክልሉ በቡና ማሣ ሽፋን ከ597 ሺህ 500 ሔክታር በላይ መድረሱን የክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ

Spread the love

‎በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቡና ልማት የተሸፈነው መሬት 597 ሺህ 521 ሔክታር መድረሱን የክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አሥራት መኩሪያ ተናገሩ።

‎በክልሉ ለቡና ልማት ምቹ ሥነ-ምኅዳር መኖሩንና ካሉት 41 የገጠር ወረዳዎች በ38ቱ ቡና በስፋት እየለማ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከወረዳዎቹ መካከል 26ቱ ቡናን ስፔሻላይዝድ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

‎በጫካ፣ በከፊል ጫካ፣ በጓሮ እና በዘመናዊ የተከላ ዘዴዎች በክልሉ ቡና እየለማ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

‎ምርታማነትን ለማሳደግም በአዲስ ማሳ ቡና ማልማትን ጨምሮ ነባር ማሳዎች ምርታማነታቸው እንዲያድግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

‎ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ጋር በማቀናጀት ባለፉት አራት ዓመታት በአማካይ በዓመት ከ68 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ በማዘጋጀት መተከሉንም ጠቅሰዋል።

‎በዚህም የቡና ማሳ ሽፋን 597 ሺህ 521 ሔክታር ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥም የጫካ ቡና 12 ነጥብ 9፣ የከፊል ጫካ 11 ነጥብ 2፣ የጓሮ ቡና 65 ነጥብ 5 እና ዘመናዊ ተከላ 10 ነጥብ 2 በመቶ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

‎በምርታማነታቸው የተሻሉ፣ በሽታ የሚቋቋሙና በተለያየ ሥነ-ምኅዳር የሚላመዱ የቡና ዝርያዎች በግብርና ምርምር ማዕከላት እና ፈቃድ ባላቸው የቡና ዘር አዘጋጅና አቅራቢ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

‎ዘንድሮ ለሚተከለው ከ86 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *