




በዳውሮ ለም መሬት ላይ እንደ ሰንደቅ ዓላማ የሚውለበለበው የእንሰት ጫካ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የህይወት ዋስትናም ነው። ከስሩ እስከ ቅጠሉ እያንዳንዱ አካሉ ለተለያየ አገልግሎት የሚውለው ይህ የክልሉ ገጸ በረከት፣ ለአንድ የዳውሮ አባወራ የብርታቱ መገለጫና የሀብቱ ማሳያ ነው። ከባህላዊው ቆጮና ቡላ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ ሆቴሎች ድረስ ተፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው።
ነገር ግን ይህ የዘመናት ሰብል ዛሬ ላይ ከባህላዊ የምግብ ምንጭነት ባሻገር ወደ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሞተርነት እየተሸጋገረ ነው። ይህን የለውጥ ጉዞ ለማየት በዳውሮ ዞን ኢሳራ ወረዳ ጉዛ ቀበሌ ወደሚገኘው የእንሰት ዘር ብዜት ጣቢያ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የጋዜጠኞች ቡድን አምርተናል።
ከዘፈቀደ አሰራር ወደ ሳይንሳዊ ምርት
በአንድ ወቅት በልማድና በዘፈቀደ ይመረት የነበረው እንሰት፣ ዛሬ በጉዛ ቀበሌ በሚገኘው የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል የቴክኖሎጂ ድጋፍ አግኝቶ ምርታማነቱ እያደገ ነው። የጣቢያው ዋና ዓላማ እንሰትን ከጓሮ ተክልነት አውጥቶ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመረት በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ነው።
የጉዛ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አበራ እንደሚሉት፣ “በማባዣ ጣቢያው የእንሰት ዘርን ‘ወንድ’ እና ‘ሴት’ በማለት ለይተን፣ በተፈጥሯዊ ማዳበሪያ በልዩ ኮሪደር እናበዛለን። ይህም ጣቢያ ለአርሶ አደሩ እንደ ማሳያና ማነቃቂያ ከማገልገሉም ባሻገር፣ ያባዛናቸውን ምርጥ ዘሮች ለአቅመ ደካሞች በነጻ በመስጠት የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና እናጠናክራለን” ብለዋል።
ከቆጮ እና ቡላ ባሻገር፡ አዲስ የገበያ አማራጭ
የኢሰራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሠለሞን ተክሌ የእንሰት ምርት እየፈጠረ ያለውን አዲስ የኢኮኖሚ አድማስ ያስረዳሉ። “እንሰት ከቆጮና ቡላ በተጨማሪ ለኬክ ምርት እየዋለ ነው። በተጨማሪም ኮባው (ደረቁ ቅጠል) እና ቃጫው ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ለግንባታ ዘርፍ ጠቃሚ ግብዓት እየሆነ ነው” ይላሉ። ይህ አዲስ አቅም አርሶ አደሩ ምርቱን በስፋት በማምረት የኢኮኖሚ አቅሙን እንዲያሳድግ ትልቅ እድል መፍጠሩን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ሲሳይ ተሰማም፣ “አርሶ አደሩ በተቀናጀ መንገድ አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን በተለያዩ አደረጃጀቶች የቴክኒክ ስልጠናዎችን በመስጠት ከጎናቸው ነን” ሲሉ የባለሙያ ድጋፉን አረጋግጠዋል።
ከትውልድ ልምድ ጋር የተዋሀደ ቴክኖሎጂ
ይህ የዘመናዊነት ሽግግር የቆየውን የአባቶች ጥበብ ያላስቀረ መሆኑን አርሶ አደር አቶ መንገሻ አለሙ ይመሰክራሉ። “ከቴክኖሎጂ በፊትም ከአባቶቻችን በቀሰምነው ልምድ እንሰትን እያመረትን ልጆቻችንን አሳድገናል። ዛሬ ላይ ደግሞ ይህንን ልምድ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር አጣምረን በስፋት ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኘን ነው” በማለት የሁለቱ ጥምረት የፈጠረላቸውን እድገት በደስታ ይናገራሉ።
በአጠቃላይ፣ በዳውሮ ዞን የሚገኘው የእንሰት ሰብል፣ በትጋትና በቴክኖሎጂ ታግዞ ከባህላዊ የህልውና መሰረትነት ወደ ዘመናዊ የብልጽግና ምንጭነት እየተሸጋገረ ያለ የአረንጓዴ ተስፋ ምልክት ሆኗል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
