




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቡና ልማት የተሸፈነው መሬት 597 ሺህ 521 ሔክታር መድረሱን የክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አሥራት መኩሪያ ተናገሩ።
በክልሉ ለቡና ልማት ምቹ ሥነ-ምኅዳር መኖሩንና ካሉት 41 የገጠር ወረዳዎች በ38ቱ ቡና በስፋት እየለማ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከወረዳዎቹ መካከል 26ቱ ቡናን ስፔሻላይዝድ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
በጫካ፣ በከፊል ጫካ፣ በጓሮ እና በዘመናዊ የተከላ ዘዴዎች በክልሉ ቡና እየለማ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም በአዲስ ማሳ ቡና ማልማትን ጨምሮ ነባር ማሳዎች ምርታማነታቸው እንዲያድግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ጋር በማቀናጀት ባለፉት አራት ዓመታት በአማካይ በዓመት ከ68 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ በማዘጋጀት መተከሉንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የቡና ማሳ ሽፋን 597 ሺህ 521 ሔክታር ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥም የጫካ ቡና 12 ነጥብ 9፣ የከፊል ጫካ 11 ነጥብ 2፣ የጓሮ ቡና 65 ነጥብ 5 እና ዘመናዊ ተከላ 10 ነጥብ 2 በመቶ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በምርታማነታቸው የተሻሉ፣ በሽታ የሚቋቋሙና በተለያየ ሥነ-ምኅዳር የሚላመዱ የቡና ዝርያዎች በግብርና ምርምር ማዕከላት እና ፈቃድ ባላቸው የቡና ዘር አዘጋጅና አቅራቢ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ዘንድሮ ለሚተከለው ከ86 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
