




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮና ተጠሪ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራት የተግባር አፈፃፀም ግምገማ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በግብርናው ሴክተር የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎችን በመምራት ከመኸር ወጥተን ወደ በልግ መሸጋገር ወቅት ላይ መሆኑንና አዲስ ኢንሼቲቪ ተቀርፆ የበጋ መስኖ ስንዴ ስራ ተግባራዊ እየተደረገ ያለበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም የአንደኛ ዙር የመደበኛ መስኖ ስራዎች እየተሰራ ያለበት ወቅት ነው ያሉት አቶ ማስረሻ በቅርቡ የበልግ ስራ የሚጀመርበት በመሆኑ እነዚህ ሥራዎች በንቅናቄ መምራት ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የግብርናና ገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን እውን የሚሆነው በገጠሩ ማህበረሰብ በተገቢው ተግባራዊ ሲደረግ ብቻ በመሆኑ ለዚህም የአመራርና ስምሪት ሂደት እና የባለሙያ ውጤታማነት ሊጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በግብርና ዘርፍ ትልቅ አቅም መኖሩን ያነሱት አቶ ማስረሻ ከዚህም አኳያ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥና ውጤት በማምጣት በሌሎች ሴክተሮችም ተመሳሳይ ለውጥ ወይም ዝላይ ለማድረግ የሚረዳ በመሆኑ በተለየ አኳኋን መምራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ጊዜ በመኸር ከተሸፈነው 370 ሺህ ሄክተር ውስጥ እስከአሁን ምርት አሰባሰብ አፈፃፀም 150 ሺህ ሄክታር መሆኑንና አፈፃፀሙን በቀጣይ የተሻለ ለማድረግ በተገቢው መገምገምና መፈተሽ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የዘንድሮው የበጋ ስንዴ ስራ ከወትሮው በተለየ መልኩ ቀድሞ ንቅናቄ በማድረግ ወደ ስራ የተገባና በአፈፃፀም ላይ ትኩረት ሊሰጠውና የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡
ከሌማት ትሩፋት ስራዎች አንጻር የተደራጁ መንደሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም ከሚፈለገው ውጤት አኳያ ብዙ መስራት የሚጠበቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሀገርቱ እና አርሶ አደሩ ከቡና ልማት በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆን የኮንትሮባንድ ቁጥጥር፣ የእሸት ቡና አዘገጃጀት እና አሸኛኘት መፈተሽ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ግብዓት አጠቃቀም የተሻለ መሆኑን ያነሱት አቶ ማስረሻ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ከአቅርቦት እና እዳ አመላለስ ጋር የሚታዩ ማነቆዎችን እየፈቱ መሄድ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ ዘላቂ የሆነ ውጤት በማምጣት አርሶ አደሩንና ሁሉንም ማህበረሰብ ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ አንድም የማይታረስ መሬት የለበትም ያሉት አቶ ማስረሻ ለዚህ እያንዳንዱ ቀበሌ በአርሶ አደር የተያዙ ይዞታዎች ታለይቶ መቀመጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አሁን ላይ የዞኖች ያለፉት አምስት ወራት አፈጻጸም እየቀረበ ሲሆን በቀረበው አፈፃፀም ላይ ውይይት በማድረግና ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ጨምሮ ሌሎች የግብርና ቢሮና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም የሁሉም ዞን መምሪያ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
