


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2017 የበጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር ባደረገው ጠንካራ ውድድር 3ኛ ደረጃን በመያዝ ታላቅ ስኬት አስመዝግቧል።
ይህ እውቅና የተሰጠው፣ ጥብቅ በሆነ ሀገር አቀፍ የአቻ ለአቻ ምዘናና ግምገማ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ላስመዘገበው ድንቅ ውጤት የማበረታቻ ሽልማትና ሰርተፍኬት ከኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እጅ ተበርክቶለታል።
ኮሚሽኑ ባስተላለፈው መልዕክት፣ ይህ አበረታችና የላቀ ውጤት ሊገኝ የቻለው በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ ተመስርቶ መሆኑን ገልጿል፦የክልሉ ጠንካራ አመራር ቁርጠኝነትና ድጋፍ፣በየተቋማቱ የተሰማሩ የሥነ-ምግባር መኮንኖች ያላሰለሰ ጥረት፣የህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎና የባለቤትነት ስሜት መሆኑን ጠቅሷል።
በመሆኑም ኮሚሽኑ ለነዚህ ሁሉ አካላት ልባዊ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ይህ ውጤት የመጨረሻው ግብ ሳይሆን ለቀጣይ የላቀ ስራ መነሳሻ መሆኑን የገለፀው ኮሚሽኑ፣ የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠልና የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የክልሉ ህዝብ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል። በተለይም የታማኝነት እሴት የሰነቀ ትውልድ በመገንባትና የተቋማትን የአሰራር ሥርዓት በማጠናከር የፀረ-ሙስና ትግሉን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ለተገኘው ውጤት በድጋሚ “እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን!” በማለት መልካም ምኞቱን ገልጿል።
