




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጤና ቢሮ 4ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እና የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሚዲያና ከህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ በታርጫ ከተማ አካሂደዋል።
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃፊው አቶ ኢብራሂም ተማም የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በክልሉ ሁሉም አካባቢ እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
4ኛ ዙር አገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከታህሳስ 3 እስከ 6/2018 ዓ.ም ለተከታታይ 4 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በክልሉ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 597,731 ህጻናትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ኃላፊው ገልጸዋል።
በመሆኑም ስለክትባቱ አስፈላጊነትን ማሳወቅ፣ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል፣ሁሉም ህፃናት ክትባቱን እንዲያገኙ ማህበረሰብን በማንቃት የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ኃላፊነቱን እንዲወጡ ጥሪ አቀርበዋል።
የማርበርግ ቫይረስ መከላከል የሚቻል ነገር ግን በአጭር ጊዜ መግደል የሚችል በሽታ መሆኑን በማስታወስ ወቅታዊ የማርበርግ ቫይረስ አሰሳና ቅኝት ተግባርም በቅንጅትና በትኩረት መሠራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ከክትባቱ ባሻገር የምግብ እጥረት ያለባቸውን ህፃናትን መለየት፣ ፣የማህበረሰብ ጤና መድኀን አገልግሎት አሰጣጥ አዲስ አባላትን የማፍራት እና ሌሎች ለጤና አገልግሎት መሳለጥ የሚያግዝ ተግባራት በማቀናጀት ውጤት ለማምጣት የኃይማኖት አባቶች ሚና የላቀ በመሆኑ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨምሳ የፖሊዮ በሽታ ክትባት 4ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለማካሄድ በቢሮው ዘርፌ ብዙ የቅድሜ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
አክለውም ፖሊዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጻናትን ለዘላቂ የአካል ጉዳት የሚዳረግ በሽታ መሆኑን ያስታወሱት ዳይረክተሩ፣ ይህን በሽታ መከላከል የሚቻለው በመደበኛ እና በዘመቻ በሚሰጡ ክትባቶች መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ለክትባት ዘመቻ ሽፋንም ሆነ ጥራት ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ በመሆኑ ይህ መድረክ መዘጋጀቱን በማንሳት በየደረጃው ያሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀርበዋል።
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እና የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋጽዮን ተረፈ ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶበታል።
ተሳታፊዎች በቀረበው ሰነድ ላይ በመወያየት በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች፣መወጣት በሚገባቸው ሚናዎችና ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄና ቅንጅት ላይ በመወያየት አቅጣጫ ላይ በመግባባት መድረኩ ተጠናቋል።
በመደረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንትና ባለሙያዎች፣ የየዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጌታሁን ግርማ
