




የደቡብ ምዕራብ ማዕድን ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፥ ኮርፖሬሽኑን በይፋ ሥራ ማስጀመር በሚቻልበት አግባብ ላይ በቦንጋ ከተማ መክሯል።
በውይይቱ ላይ የቦርድ ሰብሳቢ፥ የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፥ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ በርካታ የገፀ ምድርና ከርሰ ምድር የማዕድ ሀብት ያለበት መኾኑን በመጠቆም፥ ይህንን የማዕድን ሀብት በተገቢው በማልማት ለክልሉ ልማት ማዋል ይገባል ብለዋል።
ተግባራዊ በኾነው የሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚ ረፎርም ምሰሶዎች መካከል አንዱ ማዕድን ዘርፍ መኾኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፥ በክልሉ ለዘርፉ እመርታ ያሉ አስቻይ ሁኔታዎችን በመጠቀም ሀብቱን ለክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥና ለልማት ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግዛው ጋጊያቢ፥ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ የማዕድን ሀብቶችን በመለየት ለክልሉ ልማት ወሳኝ ድርሻ በሚኖራቸው አግባብ እንዲለሙ የሚጠቁሙ የልየታና ጥናቶች ይሰራል ብለዋል።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መነሻ የማዕድን ዘርፉ ለክልሉ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ግዛው፥ ኮርፖሬሽኑ የተጣለበትን ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የቦርድ አባላት በበኩላቸው፥ የክልሉን የማዕድን ሀብት በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለማስተዳደርና ከዘርፉ የሚገኘውን የኢኮኖሚ አበርክተው ለማሳደግ የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች ነው ብለዋል።
በዘርፉ እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት ዘመናዊ አመራር መከተል፣ የማዕድን ግብይት ሕጋዊነት እና የምርት ጥራት ማረጋገጥ እንዲሁም የመንግሥት ጥቅምን ያማከለ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባም ምክረ-ሀሳብ ቀርበዋል።
የሥራ አመራር ቦርድ አባላቶቹ፣ በኮርፖሬሽኑ የሰው ሀይል አደረጃጀት፣ የ2018 በጀት ዓመት የቀጣይ እቅድ እና በሌሎች ተቋማዊ አሰራሮች ዙርያ ሰፊ ውይይት በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በዕድገቱ በዛብህ
