


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የዳውሮ ዞን ልብ ውስጥ፣ አንድ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ተራራ የንጉሥ ሃላላ ኬላን ታሪካዊ ስፍራ ከፍ ብሎ በትኩረት የሚጠብቅ ይመስላል። ይህ በሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኘውና የአካባቢው ድምቀት የሆነው ተራራ አጦ መንትያ ይሰኛል።
ከባህር ጠለል በላይ በ3 ሺህ ሜትር ከፍታው የሰማይ ጉልላትን የሚዳስስ የሚመስለው ይህ ተራራ፣ ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነው ሰፊ ግዛቱ አስደናቂ የተፈጥሮ ሀብትን አቅፏል።
ለስፍር ቁጥር ለሌላቸው የዱር እንስሳት፣ ለውብና ብርቅዬ አዕዋፋት፣ እንዲሁም ለጥቅጥቅ ደኖችና ለምለም ቁጥቋጦዎች መኖሪያና መሸሸጊያ ሆኗል። ከወረዳው ዋና ከተማ በ8.9 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መገኘቱ ደግሞ ለጎብኚዎች በቀላሉ እንዲደርሱበት ያስችላል።
አጦ መንትያ ተራራ የተፈጥሮ ውበት ብቻ አይደለም፤ የመንፈስ እርጋታና የጸሎት ስፍራም ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ምዕመናን በተራራው ጫፍ ላይ በሚገኘው ሰፊና ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ይሰባሰባሉ። ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጁ ማረፊያዎች ውስጥ እስከ 300 ሰዎች በአንድ ጊዜ በየእምነታቸው ጸሎትና ምስጋና የሚያቀርቡበት፣ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት ቅዱስ ስፍራ ነው።
ይህንን የተፈጥሮና የመንፈስ ሀብት ለትውልድ ለማቆየት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። የወረዳው መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሀብታሙ ክፍሌ እንደተናገሩት፣ ተራራውን በተፈጥሯዊ ተክሎች የበለጠ ለማስጌጥና ለመንከባከብ በሁለት ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል።
ኦጦ መንትያ ተራራ የሃላላ ኬላን ታሪክ በዝምታ የሚተርክ፣ ለተፈጥሮ ወዳዶች አይን የሚማርክ፣ ለመንፈስ ፈላጊዎች ደግሞ የሰላም ወደብ የሆነ ድንቅ ስፍራ ነው።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
