




የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር፣ ከተማዋን በቴክኖሎጂ በማዘመን ለነዋሪዎቿ ምቹና ተመራጭ ለማድረግ ያለመውን የ’ስማርት ሲቲ’ ፕሮጀክት በተጨባጭ እርምጃ ጀመረ። ይህ ታላቅ ራዕይ እውን እንዲሆን የሚያስችለው የጥናትና ቅየሳ ሥራ፣ በከተማው ከንቲባ ኢንጅነር ሰለሞን ሌዊ እና በሌሎች ከፍተኛ አመራሮች አማካኝነት በሚዛን ጋቸብ ሰከንደሪ ሳይት በይፋ ተጀምሯል።
የከተማ አስተዳደሩ ከ”ምን ያምር ከተማ ፕላንና ተያያዥ ሥራዎች” አማካሪ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሠረት፣ በ182 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው ይህ ጥናት የሚዛን አማንን የወደፊት ገጽታ ለመቅረጽ የመጀመሪያው ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
የከተማው ከንቲባ ኢንጅነር ሰለሞን ሌዊ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ “ስማርት ሲቲ ማለት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጣችንን የሚያዘምን ነው” ብለዋል። ሚዛን አማን ይህንን ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመተግበር በክልሉ ካሉ ከተሞች ቀዳሚ መሆኗን የገለጹት ከንቲባው፣ ይህ የጥናት ጅማሮ የፕሮጀክቱ ትልቁ ማሳያ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ የ’ስማርት ሲቲ’ ጥናት አሁን በተጀመረበት ብቻ ሳይወሰን በቀጣይነት የሸኮ በርና የአማን ኤርፖርትን አካባቢዎች ማዕከል አድርጎ እንደሚቀጥልም ተገልጿል። የአማካሪ ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፋናዬ ታደሰ በበኩላቸው፣ ጥናቱን በሦስት ወራት ውስጥ አጠናቀው እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል።
የከተማው ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ታገል ወንድሙ፣ ፕሮጀክቱ ከፌደራል መንግስት ጀምሮ በተሰጡ ተከታታይ ሥልጠናዎች የታገዘ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ተግባር መገባቱ የዝግጅቱን ውጤታማነት ያሳያል ብለዋል።
በተመሳሳይ የከተማው ዋና ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር በረከት ምናሴ፣ ጥናቱ ከተማዋን በፕላን ለመምራት፣ የመሬት አጠቃቀምን ለማዘመን፣ ስሉጥ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋትና በICT የተደገፈ ቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ የጥናት ምዕራፍ ሲጠናቀቅ የሚዛን አማን ከተማ ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥን በመተግበር በክልሉ ቀዳሚና ለአብነት የምትጠቀስ ከተማ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል ሲል ቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።
