ስር የሰደዱ ችግሮችን አሸንፈን ወደ እውነተኛ ብልጽግና እየገሰገስን እንገኛለን፦ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር )

Spread the love

“የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሃሳብ በሐረር ከተማ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የመደመር መንግስትና ፓርቲያችን ስር የሰደዱ ችግረኞችን በመቅረፍ፣ የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር ወደ ስኬት ጎዳና እየተንደረደርን እንገኛለን ብለዋል ።

ፓርቲያችን ፈተናዎችን እየተሻገረ ፈጠራን መሰረት በማድረግ ፍጥነትን ያማከለ ስራዎችን በመስራትና ከህዝባችን የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።

በሀገራችን ታሪክ የዲፕሎማሲ የበላይነትን ያረጋገጥንበትን ፣ የውጭና የውስጥ ጫናዎችን ተቋቁመን አባይን የገደብንበትን ድል በማሰብ የቀጣይ የቀጠና አውዳችንን ለማስፋት ውጥን መያዝን አላማን ያደረገ መድረክ ነው ብለዋል።

የህዝባችንን ቅቡልነት ለማግኘት በህዝባችንና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት የተሻለ ለማድረግ እድል የሚፈጥር መድረክ እንደመሆኑ የህዝባችንን ሀሳብና ጥያቄዎች ወደ ተግባር የምንለውጥበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በቱሪዝም ዘርፉ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የገለጹት ዶክተር ነጋሽ ለዚህም የሐረር ከተማ ማሳያ ናት ብለዋል።

እንደ ዶክተር ነጋሽ ገለጻ በከተማው ዘርፍ በኮሪደር ልማት የጀመርናቸው ስራዎች አመርቂ ውጤቶች እያሳዩን ይገኛል።

በግብርና ዘርፍ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉንና በሌማት ቱሩፋት አሻራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለናልም ብለዋል።

በተለይም በሐረር ከተማ የተሰሩ አመርቂ የልማት ስራዎች የክልሉ አመራሮች ምን ያህል ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው መስራታቸውን ማሳያ ናቸው ነው ያሉት።

በመጨረሻም ፓርቲው የጀመራቸውን ሁሉን አቀፍ የልማት እቅዶች ለማሳካት ፈጠራና ፍጥነትን በማከለ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃልም ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የሐረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል ሲል የሀረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *