




በግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የጣሎ ወረዳ ግብርና ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አፋወርቅ አደመ በአካባቢውን ያለውን ፀጋ በመጠቀም በወረዳው በዓመት ከ2300 ሄክታር በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት 320ሺ ኩንታል በላይ ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህም በመነሳት ከአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ጋር በማስተሳሰር በዘርፉ ለወጣቶች የሙያ ድጋፍና ስልጠና በመስጠት የስራ ዕድል በመፍጠር ራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ ከመደረጉም በላይ ለሌሎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተሞክሮ ማሳየቱን አንስተዋል።
በተሰራው ስራ በግብርናው ዘርፍ የቤተሰብን መሬትን በሙዝና ቡና በመሸፈን እንዲሁም ንብ በማነብ ለአካባቢው ወጣቶች ሞዴል የሆነ ወጣት ታጋይ ገ/ሚካኤልን ለአብነት ጠቅሰዋል፡
ወጣት ታጋይ ገ/ሚካኤል የጣሎ ወረዳ ሻዳ ቀበሌ ነዋሪ ነው ። ወጣቱ ታጋይ በ2012 ወቅቱ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ ባለበት ወቅት በኮቭድ ቫይረስ ምክንያት ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ለእረፍት ወደ ቤተሰብ መምጣቱን ያስታውሳል።
በወቅቱ በውስጡ ቁጭት በማሳደሩ በ2013 ዓ/ም ከአርባምንጭ ዩኒቨርሰቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ከተመረቀ በኃላ በሚማርበት አካባቢ ያየውን ተሞክሮ በመውሰድ ጥቅት የሙዝ ዝሪያ ችግኝ ከአርባምንጭ በማምጣት ስራ መጀመሩን ይገልጻል።
ዓላማውን የአካባቢውን ስነ ምህዳሩን ከመጠበቅና ኢኮኖሚን በማመንጨት ስራን ከመፈለግ ወደ ስራ ፈጣሪነት መግባቱን ያስታውሳል ።
በመሆኑም አሁን በቤተሰብ ማሳ 0.6ሄክታር እና ከመንግሥት በወሰደው 0.4 በአጠቃላይ አንድ ሄክታር ሙዝ በማልማት ከ100ሺ ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን እንዲሁም ከማር ምርት 15ሺ ብር ማግኘቱን ገልጸዋል።
አክለውም በቤተሰብ ይዞታ 2 ሄክታር ቡና ባለማው ከ100ሺ ብር በላይ ማግኘቱን በማስታወስ በዚህ የምርት ዘመን ከደረሰው የቡና ምርት 500ሺ ብር በላይ ለማግኘት አቅደው ምርትን በማሰባሰብ ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቡና፣ ሙዝና ከንብ እርባታ ባገኘው ሀብት የተለያዩ የማስፋፊያ ስራ እየሰራ መሆኑን ያነሳው ወጣት ታጋይ የዶሮና እንስሳት እርባታ እና ሌሎች የቅመማ ቅመምና የመኖ ልማት ስራ መጀመሩን ነው የገለጸው።
በስራው ውጤታማና ደስተኛ መሆኑን ያነሳው ወጣት ታጋይ ከራሱ ሀብት ከማፍራት ባሻገር ለ6 ቋሚና 6 ጊዜያዊ ሠራተኞች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አንስተው የአካባቢው ወጣቶችም ይህን በማየት ወደ ስራ መግባታቸውን ይገልጻል።
ይህ ራሱን ከመቻል አልፈው ለሌሎች የአካባቢ ወጣቶች አርአያ መሆኑን በመግለፅ አሁን የስራ እንቅስቃሰን በማየት ወረዳው በማህበር በማደራጀት በሰጠው 8ሄክታር መሬት ቡና፣ ሙዝ፣ የንብ እና የእንስሳት እርባታን በማስፋት ከአካባቢው ፍጆታ አልፈው ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለመጫን አቅደው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
በተፈጠረው የስራ ዕድል ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት ታደለ እምቶ እና ወ/ሮ አበዛሽ አደሎ ገቢ በማግኘት ቤተሰብን ከማስተዳደርም በላይ ባገኙት ተሞክሮ በማሳቸው ቀጣይ ሀብት ለማፍራት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጌታሁን ግርማ
