


የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የድጋፍና ክትትል ቡድን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከቢሮ ኃላፊዎችና ማናጅመንት አካላት ጋር ተወያይተዋል።
የድጋፍና ክትትል ቡድን ዓላማዉ፤ ክልላዊ የኮሙኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ያለበት ደረጃ በመገምገም ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እንዲሁም ክፍተቶችን በመሙላት የቀጣይ ሥራዎች የተቀላጠፈ እንዲሆን ለማስችል ነዉ።
የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ድጋፍ ቡድን፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተጀመሩትን መልካም የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ሥራዎች በማድነቅ፣ ቀጣይ ጥረቶችን ለማጎልበት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።
የአገልግሎቱ የድጋፍና ክትትል ቡድን በክልሉ ባደረገው ምልከታ፣ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የሚሰጡትን ግብረመልሶች በመቀበል ክፍተቶችን ለማረምና ጥንካሬዎችን ለማጎልበት የሚያደርገው ጥረት በጎ እንቅስቃሴ መሆኑን ገልጿል።
በተለይም ተቋሙ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ተጠቅሞ ለህብረተሰቡ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አበረታች እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ስኬት ለማስቀጠል ይዘቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ሥራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ተመላክቷል።
በቀጣይ ሀገራዊና ክልላዊ ገጽታን የሚገነቡ እንዲሁም የልማት ሥራዎችን የሚያስተዋውቁ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ህብረተሰቡን የመረጃ ባለቤት ለማድረግ የተጀመረዉ ሥራ እንዲጠናከር ጠቅሰዋል ።
ለዚህም ስኬት ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ፣ የአጀንዳ ቀረጻና የይዘት ዝግጅትን ማዘመን፣ እንዲሁም የመንግስት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ማድረግ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫነት ተለይተዋል።
የፌደራል መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የድጋፍ ቡድን እነዚህን የጋራ ግቦች ለማሳካት በክልሉ የሚታዩ የባለሙያዎችን የአቅም ግንባታ እና የግብዓት ፍላጎቶችን ለመፍታት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
በክልሉ በየደረጃው ከሚገኙ ኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ተቋማት የመረጃ ሥርጭት ወጥነት እና የተናበበ ለማድረግ የተለኀኀያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ናቸዉ።
በክልሉ በሚገኙ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እንዲሁም ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ተቋማት እና ኮሙኒኬሽን መዋቅሮች ጋር የሚዲያ ሥራዎችን የሚያቀላጥፍ የጋራ የሚዲያ ፎረም ተቋቁመው ሥራዎች በተቀናጀ እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ለኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ተቋማት የአጀንዳ ጥቆማ በመስጠት ውጤታማነትን እየገመገመ የመሄዱ ሂደት መኖሩን ጠቅሰዉ ይኸዉም ውጤታማ ሥራዎች እንዲከናወኑ እያስቻለ በመሆኑ በተጠናከረ ይቀጥላል ብለዋል ኃላፊው።
ከሁነት ተኮር ወደ ዓላማ ተኮር የመሸጋገር ዓላማ ይዘዉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዘቶችን በመቅረጽና በማዘጋጀት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነዉ የገለፁት።
ተቋሙ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በማስፋት ከእነዚህ ባህር ጋር ተሰማሚነት ያላቸው ይዘቶችን አዘጋጅቶ ማሰራጨት፣ በሚዲያ ሞኒተሪንግና ህዝብ አስተያየት እንዲሁም የሚዲያ ሠራዊትና ሌሎች መረጃዎችን የማደራጀት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኃላፊው ጠቅሰዋል።
ይህ ድጋፍና ክትትል በክልሉ የተጀመረውን ውጤታማ የኮሙኒኬሽን ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰው ታምኖበታል።
በፍቅር ከበደ
