ከመማር ማስተማር ተግባር በተጓዳኝ በግብርና ሥራ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የኢሞታ ትምህርት ቤት አስታወቀ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በኮንታ ዞን የሚገኘው የኢሞታ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በግብርና ሥራ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን መመልከት ተችሏል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ያዕቆብ ከተለ፥ ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ በዞኑ ልማት ማኅበር ስር እንደሚተዳደር በመግለጽ፣ ከመማር ማስተማር ተግባር ጎን ለጎን በሚያከናውነው የግብርና ልማት ሥራ ውጤታማ ነው ብለዋል።

በመደበኛ የመማር ማስተማር ተግባር፣ ትምህርት ቤቱ ግንባር ቀደም ተማሪዎች ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ በመቀበል አሁን ላይ 11ኛ ክፍል ማድረስ መቻሉን በማንሳት አጠቃላይ የተማሪዎች ብዛትም 94 መኾኑን ገልጸዋል።

ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ገቢ በስፋት የሚከናወነው የእርሻ ሥራ የተማሪዎችን ቀለብ ከመሸፈን አልፎ ተጨማሪ ገቢን ለትምህርት ቤቱ እያስገኘ እንደኾነም ነው ርዕሰ መምህሩ የገለጹት።

ትምህርት ቤቱ ከተማሪዎች ፍጆታ የሚተርፈውን ምርት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እያስቻለ መኾኑን የገለጹት አቶ ያዕቆብ፥ በቀጣይም የግብርና ሥራውን ለማስፋት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ ከግብርና ስራዎች በተጨማሪነት የውጭ ዝሪያ ያላቸውን የወተት ላሞች በመያዝ በእንስሳት እርባታ ዘርፍም ውጤታማ ተግባራት እየተከናወነ ስለመኾኑም ርዕሰ መምህሩ አብራርተዋል።

በዚህም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሁለቱም ዘርፍ ከ350 ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለጹት አቶ ያዕቆብ፥ በሂዴቱም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ቤቱ የሚከናወነው የግብርና ሥራ ለአከባቢው ማኅበረሰብ ምሳሌ የሚኾን ነው ያሉት ርዕሰ መምህሩ፥ የእንስሳት እርባታ ሥራን በማስፋት ለአመያና የጭዳ ከተሞች ምርቱን በስፋት ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *