ሪፖርታዥ

Spread the love

በክልሉ የግብርና ልማት ግቦች እንዲሳኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ ፕሮግራም ፦

በክልሉ ግብርና ቢሮ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ብሎም የዜጎችን የስነ ምግብ ስርዓትን ለማሻሻል እና በዘርፉ የስራ ዕድል ለመፍጠር ዘርፌ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፤ በዚህም በዘርፉ አበረታች ውጤትም እየተመዘገበ ይገኛል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የክልሉን የመልማት አቅም በመለየት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማስረጽ፣ የኤክስቴንሽን ስርዓቱን በመዘርጋት የክልሉ የዜጎችን የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የገቢ አቅም ማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም ማኅበረሰብ የመፍጠር ዓላማዎችን በመያዝ ተግባራትን አቅደው በማከናወን ላይ ይገኛል።

በክልሉ የግብርና ልማት ስራዎችን ከሚደግፉና ግቦች እንዲሳኩ የበኩሉን ድርሻውን ከሚወጡ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ ተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግር (PACT) ፕሮግራም በእንግልዘኛው (Participatory Agriculture and Climate Transformation) ነው።

በመሆኑም በዛሬው ቆይታችን ከክልሉ የግብርና ቢሮ ጋር በቅንጅት ከሚሰሩት ፕሮግራሞች አንዱ የሆነውን ተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግር (PACT) ፕሮግራም ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉና የተከናወኑ የተግባር አፈጻጸምን ለመቃኘት ወደድን። መልካም ንባብ፦

ፕሮግራሙ በክልሉ በዳውሮና ምዕራብ ኦሞ ዞን በ3 ወረዳዎች 5ሺ አባዎራ/እማወራ ደረጃ 25ሺህ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ የሚገኝ ነው።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርናና አየር ንብረት ሽግግር (PACT) ፕሮግራም ማናጀር አቶ ታመነ ተስፋዬ ፕሮግራሙ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ደህንነትን በመቀነስ፣ የአርሶ አደሩን ኑሮ የሚያሻሽሉና የምግብና ስርዓተ- ምግብ ዋስትና ችግርን የሚያቃልሉ ተግባራትን በፕሮግራሙ በተመረጡ የመሬት ገጽታዎች (Landscapes) ላይ እያከናወነ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሦስቱ የፕሮግራሙ የትኩረት መስኮች (Componantes) :- አሳታፊ የአየር ንብረት ለዉጥ ሥራዎችን በማካሄድ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ (Community-Led Climate-Smart Productive Land scopes)፣ የህብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀት እና ገበያ ልማት ሥራዎች ላይ ድጋፍ ማድረግ (Agribusiness Development and Market Linkage)፣ ተቋማዊና የፖሊሲ ማጠናከሪያ ሥራዎች እና በአተገባበር ላይ ድጋፍ ማድረግ (Institutional and Policy Strengthening Implementation Support Services) እንደሆነም አክለዋል።

በዚሁ መሰረት ፕሮግራሙ በሥነ-አካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ሥራዎች፣ በሆርቲካልቸር ሰብሎች ልማት፣ ችግኝ ጣቢያዎች ማቋቋም፣ የአነስተኛ መስኖ አውታሮችና የእህል ማከማቻ መጋዘኖች ግንባታ፣ የአሲዳማ መሬት ማከም፣ እንዲሁም የሌማት ትሩፋትን ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት እንደሚያከናወን ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ በሚከናወኑ ተግባራቶች ሁሉ የሴቶች ተሳትፈና ተጠቃሚነት 50% ፣የወጣቶች 40% እንድሁም የአካል ጉዳጠኞች 15% ሆኖ መከናወን እንዳለበትም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደምሰራ ገልጸዋል፡፡

አክለውም በስርዓተ ፆታ ዙሪያ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የሥርዓተ ጾታ መልካም አርአያ ቤተሰብ በመፍጠር ሴቶች ፣ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በአስተሳሰብና በተግባር ለውጥ በማምጣት በተለይ የሴቶችን የስራ ጫና ከመቀነስም በላይ በፕሮግራሙ፣ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ መደላደል እየፈጠረ ያለ ፕሮግራም መሆኑን ማናጀሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ የዝግጅት ምዕራፉን በማጠናቀቅ በ2017 ዓ/ም ወደ ተግባር የገባ ሲሆን፦ በብርዕ ሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በመጠበቅና በማልማት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የመሠረተ ልማት ግንባታዎች(የመስኖ ልማት አውታር፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታና ጥገና፣ የህብረት ስራ መጋዘንና የገበያ ማዕከል ግንባታዎች)፤ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ስራዎች፣ የስርዓተ ምግብ ማሻሻያ ስራዎች፣የስርዓተ -ፆታ ሞዴል ቤተሰብ መፍጠር ላይ አሻራውን እያሳረፈ መሆኑን አቶ ታመነ አብራርተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠርን ቁልፍ የልማት ትኩረት አቅጣጫ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።

እነዚህ ተግባራትም በተመረጡ በአምስት የመሬት ገጽታዎች (Landscapes) የሚታየውን ደህነትንና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን መጠን በመቀነስ ገቢያቸውን፣የምግብና ስነ ምግብ ዋስትና በዘላቂነት እንዲሻሻል ማስቻል እንደሆነም አክለዋል።

በተጨማሪም ፕሮግራሙ የአርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤቶችን (farmers filed school (FFS) በማቋቋምና በመደገፍ የአርሶ አደሩን የመመራመርና የመማማር አቅምን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ፤ በ3ቱ የፕሮግራም ወረዳዎች የተፈቀደውን 5 መሬት ገጽታ (Landscapes) የመለየት፣ መስፈርቱ መሠረት በማድረግ ከ5 የመሬት ገጽታ 5ሺ ተጠቃሚዎችን ምዝገባ ማካሄድ፣ ለተመዘገቡት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።

በ3ቱ የፕሮግራም ተጠቃሚ ወረዳዎች ለአነስተኛ መስኖ ግንባታ የሚውል ውኃዎችን የመለየት ስራ ማከናወኑን፤ 2 አዲስና 3 የጥገና ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ግንባታ ጥናትና ዲዛይን ስራዎችን ማጠናቀቁን አቶ ታመነ ገልጸዋል።

አክለው በ3 ወረዳዎች የአቮካዶ ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም 62,900 የተሻሻለ ችግኝ በማፍላት በኩታገጠም የማስተከልና የማልማት፤ በተቋቋመው የችግኝ ጣቢያዎች ለ45 ወጣቶች የስራ ዕድል የመፍጠር ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።

በቁጥር 42 የአርሶ አደር ትምህርት ቤቶችን 1344 አርሶ አደር አባላትን የያዘ ቡድን በማቋቋም የቡድን ኤክስቴንሽን ስርዓትን በማጠናከር የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ በምርት ሂደቱ የሚያጋጥሙትን ማነቆዎችን በራሱ መንገድ እንዲፈታና ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድግና የገበያ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ የግብርና ልማት ግቦቻችን እንዲሳኩ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ዕውን በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አንስተው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ለፕሮግራሙ ግቦች መሳካትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *