






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት የህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረሃይል ምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የምክክር መድረኩ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነዉ።
በዚሁ መድረክ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ በየደረጃው የምርቶች አቅርቦትና ዝውውር ሥርጭት እንዲሁም ወደ ማዕከላዊ ገበያ እና ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩ ምርቶች የተሳለጠ እንዲሁም ጤናማ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል ግብረሃይል ተቋቁመው ሥራዎች ሲሰሩ ቆይቷል።
በክልሉ የተቋቋመው የህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ግብረሃይል ጤናማ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ያነሱት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚህም በህገወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።
በክልሉ የወርቅ ምርት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ግብረሃይሉ ጋር በተጠናከረ መልኩ በተሰራው ሥራ እጥፍ የወርቅ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ማግኘት ተችሏልም ብለዋል።
በህገ-ወጥ ስራዎች ላይ የተሰማሩ አካላትን ተጠያቂ በማድረግና እርምጃ በመውሰድ በነዳጅ፣ በወርቅ እና በፍጆታ እቃዎች ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መቀነስ መቻሉንም አንስተዋል።
በቡና ምርት ግብይት ላይም ቁጥጥር በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው ፤ ግብረ-ኃይሉ በዞን እና በክልል ደረጃ የሚሰራቸውን ውጤታማ ስራዎች በታችኞቹ መዋቅሮችም ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በማከልም ርዕሰ መስተዳድሩ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ግብረሃይል ተቋቁመው በተሰራው ጠንካራ ሥራ ውጤቶች እየተመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ በበኩላቸው ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት እንዲሁም ከክልል አልፎ ወደ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር የሚላኩ ምርቶች በስፋት የሚመረትበት አከባቢ ነው።
በክልሉ ጤናማ የንግድና የገበያ ሥርዓት እንዲኖር ክልላዊ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የመከላከል እና መቆጣጠር ግብረሃይል ተቋቁመው እየተሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ታሪኩ አካሉ የገለጹት።
ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ዙሪያ የተዘጋጁ ሰነዶች በክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትልና የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምዴ ፋሪስ እና በቢሮ ምክትልና የገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አሰገደች ወ/የስ እያቀረቡ ይገኛሉ።
በዚሁ መድረክ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
በፍቅር ከበደ
