




የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እርካታ ጨምሯል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተቋቋመው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታ መሆኑን ተገልጋዮች ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት ከቢሮ ቢሮ መመላለስና ረጅም ጊዜ መቆየት የተለመደ ነበር። አሁን ግን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሚዛን አማን ከተማ የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይህንን ታሪክ እየቀየረው ነው። ፈጣን፣ ቀልጣፋና ያለ ምንም እንግልት አገልግሎት እያገኘን ነው ሲሉ ተገልጋዮች በደስታ ይናገራሉ።
በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ይህ ዘመናዊ ማዕከል፣ 35 የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር በማጠቃለል የሕዝቡን ድካም አቅልሏል።
በማዕከሉ ካገኘናቸው ተገልጋዮች መካከል አንዱ የሆነው አቶ ሰለሞን ዶቼ፣ በጣም ፈጣንና ምንም ማጉላላት የሌለበት አገልግሎት ነው ያገኘሁት፤በደቂቃዎች ውስጥ ጉዳዬን ጨርሼ ወጥቻለሁ ፤ እጅግ ደስተኛ ነኝ በማለት ተናግሯል።
ሌላኛው ተገልጋይ አቶ አህመድ መሐመድም አገልግሎቱ በጣም የተሻለ ነው፤ ይህ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ መልዕክቱን አስተላልፏል።
በተለይ ወጣቶች እንደገለጹት፣ በማዕከሉ ውስጥ ሁሉም አገልግሎት የሚሰጠው በተራ እና በቲኬት ቁጥር አላስፈላጊ አሰራርን በማስቀረት ለእኩልነትና ለግልጸኝነት በር ከፍቷል ሲሉ ጠቅሰቀል።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስራት አዳሮ እንደሚሉት፣ መሶብ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ አካል ነው። በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩትን እንግልት፣ ተደጋጋሚ ምልልስና የብልሹ አሰራር ችግሮችን ለመቅረፍ የተዘረጋ ስርዓት ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ከተበታተነ አሰራር ወጥቶ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ከማሰባሰቡም በላይ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የኦንላይን አገልግሎት በመስጠት ወደ ዲጂታል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መሸጋገሩን አቶ አስራት አስረድተዋል። እስካሁን ባለው አጭር ጊዜ ውስጥም ከ6 ሺህ 454 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሕዝቡ ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ያለምንም ስጋት አገልግሎት እንዲያገኝ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
