




በቢሮው ከፍተኛ አመራሮች የተመራ ልዑክ በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ የሚሠሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን ሱሪ ወረዳ የሚሠሩ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ የልማት እና የፕሮጀክት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና በዘላቂነት የተረጋጋ ኑሮ እንዲመሩ በክልሉ መንግሥት በኩል ሰፊ ስራ እየተሠራ መሆኑን የአርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ኋላፊ አቶ መቱ አኮ ተናግረዋል።
ሱሪ ወረዳ ለተለያዩ የሰብል ልማቶች ብሎም ለእንስሳት እርባታ፣ ለማዕድን ልማትና ለቱሪዝም ዘርፍ ምቹ መሆኑን የተናገሩት አቶ መኩ ይህን ዕድል በዕውቀት በመምራት እና ሰው ተኮር በማድረግ ይበልጥ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ብለዋል።
በተለይ በቢሮው በኩል የሚደገፉ የመንገድ፣ የእንስሳት ጤና ክሊኒክ፣ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች እንዲሁም በወረዳው የሚገኙ ፕሮጀክቶች እና ፕሮግራሞች ዘላቂ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ በመስክ ምልከታው ወቅት አቶ መኩ አሳስበዋል።
ግብርናው የአርብቶ አደሩን ኑሮ በሚቀይር መልኩ በሚታይ እና ዘላቂነት ላይ ተመስርቶ እንዲሠራ የማሳያ ስራዎች ውጤታማነት መረጋገጥ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ በሁሉም ዘርፎች የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር የሚሠሩ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።
የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ መንግሥት የ2018 ኢንሼቲቮች መካከል አንዱ የሆነው በአንድ ወረዳ የአንድ ሞዴል ቀበሌ የመመስረት ተግባር በሱሪ ወረዳ ውጤታማ በሚሆንበት ዙሪያም ከወረዳው አስተዳደር ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የቢሮው ምክትልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ዘርፍ ኋላፊ ዶ/ር ታጠቅ ብርሃኑ በበኩላቸው የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚሠሩ የልማት ስራዎች የአካባቢውን ስነ ምህዳር የተከተሉና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ልሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይ ሱሪ ወረዳ ለአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ምቹ በመሆኑ አርብቶ አደሩን ወደ እርሻ ልማት ለማስገባት እንዲቻል ሠርቶ ማሳያ ቦታዎች ውጤታማነታቸው ልረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውይይቱም የሱሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባርዱላ ኦላቡሰኒ የመንግሥት ዕቅዶችን ወደ መሬት ከማውረድ አንጻር የወረዳው አስተዳደር ብዙ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ለስኬታማነቱም በየደረጃው የሚገኙ አካላት ክትትል እና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በሁሉም የልማት ዘርፎች በወረዳው የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የወረዳው አስተዳደር በቀጣይነት አተኩሮ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የሞዴል መንደር ምስረታ ስራው በዋናነት በቱልጊት ቀበሌ የተጀመረ ቢሆንም የወረዳው አስተዳደር በወረዳው ሦስት ቀበሌዎችን በመምረጥ ሞዴል ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወረዳው የበርካታ መስህብ ስፍራዎች ባለቤት መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው አካባቢውን ከማስተዋወቅ አንጻር ከክልሉ ሚዲያ ጋር በቀጣይ አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግርዋል።
በወረዳው ክቢሽ ከተማና አካባቢው በክልሉ አርብቶ አደር እና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ድጋፍ እየተሠሩ ያሉ የልማት ስራዎች፣ የሞዴል አርሶ አርብቶ አደር ማሳዎች፣ በግንባታ ላይ ያለ የእንስሳት ህክምና ክልኒክ፣ የቱሪስት ማረፊያ ስፍራና እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የተጎበኙ ሲሆን የቢሮው ኋላፊ አቶ መቱ አኮን ጨምሮ የቢሮው ምክትሎች እና የየዘርፉ ኋላፊዎች እንዲሁም የሱሪ ወረዳ አመራሮችና የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ቡድን አባላት መሳተፋቸዉን የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርኩ ዘግቧል።
