gbhtg

Spread the love

ሞዴል አርሶ አደር ደነቀ ሳኒሞ ነዋሪነታቸው በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ ኤላ ባቾ ቀበሌ ሲኾን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በንብ ማነብ የግብርና ዘርፍ ሥራ መሰማራታቸውን ይገልፃሉ።

ምንም እንኳን ንብ ማነብ ከጀመሩ ረዥም ጊዜ ቢኾናቸውም የተሟላ የመንግሥት ድጋፍ በወቅቱ ስላልነበረ ተገቢውን ጥቅም እያገኙ እንዳልነበረ በማስታወስ አሁን ላይ መንግሥት እያደረገ በሚገኘው ድጋፍ ምርታማነቱ በዕጥፍ ጨምሮ ውጤታማ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ባህላዊ የንብ ቀፎዎች ብቻ ሰቅለው ውስን የማር ምርት ያገኙ እንደነበር የገለጹት አርሶአደር ደነቀ አሁን ላይ በአከባቢው በ12 የተለያዩ ቦታዎች ከ1መቶ በላይ ዘመናዊና ከ1ሺህ በላይ ባህላዊ ቀፎዎችን በመስቀል የተሻለ የማር ምርት እያገኙ እንደኾነ ተናግረዋል።

በተለያዩ ቦታዎች የንብ ቀፎ መሰቀሉ የሚገኘው የማር ምርቱ በአየር ፀባይ የሚወሰን መኾኑን የገለጹት አርሶአደሩ በአመት ከማር ምርት ከአራት መቶ ሺህ ብር ገቢ እያገኙ እንደኾነ አስረድተዋል።

የማር ምርቱን ከአዲስ አበባ ነጋዴ ተቀብሎ በቀጥታ ወደ ጣሊያን ሀገር ገበያ በዓመት እስከ 3 ጊዜ እንደሚልክ የገለጹት አርሶአደር ደነቀ በዚህም የተሻለ የገበያ ትስሰር በመፈጠሩ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የንብ ማነብ ስራ ልዩ ጥንቃቄን የሚሻ መኾኑን በማንሳት የባለሙያዎችን ድጋፍ በተገቢው ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው በዘርፉ ውጤታማ እንደኾኑ አስረድተዋል።

በወረዳው በተበታተነ መልኩ የሚሰራውን የንብ ማነብ ሥራ በማር መንደር ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት ምርታማነቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የፕላንና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ በላቸው፥ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በወረዳው የማር ምርታማነት ማደጉን ተናግረዋል።

በወረዳው እያንዳንዳቸው 20 አርሶአደሮችን ያቀፉ 10 የማር መንደሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ባህሩ በእነዚህ የማር መንደር ምርታማነትን ለማሳደግ የሽግግርና የዘመናዊ ቀፎ ፣ የማር ማጣሪያ እና የንብ መነቢያ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የሞዴል አርሶ አደሩን ተሞክሮ የተከተሉ በወረዳው የሀሊአኒ አይሺ እና ኤላ ባቾ ቀበሌ አርሶ አደሮችም በንብ ማነብ ሥራ ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኙም የወረዳው የግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት የንብና ሐርልማት ባለሙያ ሙሉነሽ ከበደ ገልጸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *