









በክልሉ የህዝቦች ባህል፣ ታሪክ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲጠናከርና ህብረብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት እንዲሁም የሀገሪቱ የሠላም ዕሴት ግንባታ እንዲሳካ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ የሆኑት የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት፤ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ፤ የህዝቦች ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማፅናት ብሎም የሰላምና የልማት ትብብሮችን ከማጠናከር ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡
መንግስት ህዝቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉና እንዲያለሙ ከመደገፍ ባለፈ ህዝባዊ በዓላት ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው የህዝቦች ትስስርን በሚያጎለብቱ አግባብ እንዲከበሩ እንዲሁም በአግባቡ ተዋውቀውና ዓለምአቀፍ ዕውቅና አግኝተው የቱሪዝም ሀብት እንዲሆኑ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በዛሬው “ቆይታ ከእኛ ጋር” ዝግጅታችን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተከበሩ ያሉ የብሔር/ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት አከባበርን በሚመለከት ከክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ከአቶ ፋንታሁን ብላቴ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
መልካም ንባብ!
መንግስት ኮሙኒኬሽን፡- በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!
*አቶ ፋንታሁን፦ እኔም ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳችሁ ስላደረጋችሁን አመሰግናለሁ!
*መንግሥት ኮሙኒኬሽን፦ የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ምን ይመስላሉ አከባበራቸውስ እንዴት ነው?
*አቶ ፋንታሁን ብላቴ፦ በክልል ከተደራጀን ወዲህ በባህል ዘርፍ ትልቅ ለውጥ መጥቷል። ከነዚህም ለውጥ ከመጣባቸው የባህል ዘርፎች አንዱ የክልሉ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት አከባበር ነው ።
ክልሉ እራሱን ችሎ ከመደራጀቱ በፊት በክልሉ ያሉ ብሔር/ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት አከባበር ብዙም ጎልቶ የወጣ እንዳልነበረም። የክልሉ መደራጀት ብሔሩ/ብሔረሰቡ የራሱን ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ከማልማት ረገድ ትልቅ ሚና አለው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 13 ነባር ብሔር/ብሔረሰቦችና በርካታ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተቻችለው እና ተከባብረው የሚኖሩበት የበርካታ ውብ ባህሎችና ስርዓቶች ባለቤት የሆኑት የክልላችን ህዝቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ የዘመን መለወጫ በዓላት ባለቤትም ናቸው፡፡
ከእነዚህም ከነሐሴ እስከ ጥር ሃያዎቹ ድረስ የዳውሮ፤ የኮንታ፣ የካፋ፣ የሸካ እና የቤንች ሸኮ ዞኖች ህዝቦች የዘመን መለወጫ በዓሎቻቸውን በልዮ ድምቀት፤ በራስ ቀለም አምረውና ተውበው፤ በአደባባይ አሸብርቀው ያከብራሉ፡፡
በዓላቱ እንደ የብሔር/ብሔረሰቡ ትውፊት፤ ባህላዊ ዕሴትና የጊዜ ቀመር፡- በዳውሮ ‘ቶክበኣ’፣ በኮንታ ‘ህንግጫ’፣ በካፋ ‘ማሽቃሮ’፤ በሸካ ‘ማሽቃሬ ባሮ’፣ በቤንች ህዝቦች ዘንድ ‘ብስት ባር’ እንዲሁም በሸኮ ህዝብ ‘ቲካሻ ቤንጊ’ በሚል መጠሪያ በልዩ ድምቀት የሚከበሩ ድንቅ የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡
ብሔር/ብሔረሰቦቹ የዘመን መለወጫ በዓላቱን በሚያከብርበት ወቅት አሮጌውን ዓመት ሸኝተው፤ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስና በአዲስ ጉልበት ተሞልተው ለላቀ ስኬት የሚነሳሱበት ጭምር ነው፡፡
በአከባበር ስርዓታቸውም፤ የህዝቦችን ዘመናት የተሻገረ አብሮነት፤ የእርስ በርስ ትስስርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሚያንፀባርቁ፤ የሰላምና የአንድነት፤ የኅብረትና የወንድማማችነት መርህን በመከተል የእርቅ፤ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የመተሳሰብ ዕሴቶችን በሚያጎለብቱ የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶች በአብሮነት በድምቀት ያከበራሉ።
*መንግሥት ኮሙኒኬሽን፦ የብሔር/ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት በየዓመቱ መከበር በክልሉ ህዝቦች ዘንድ ያለው ተፈላጊነት እና የሚኖረው ባህላዊና ታሪካዊ ፋይዳው ምንድነው?
*አቶ ፋንታሁን፦ በክልሉ በሁሉም ብሔር/ብሔረሰቦች ዘንድ የዘመን መለወጫ በዓላቱ ሲከበሩ መቻቻልና አብሮነት የሚጎለብትበት፤ ፍቅርና መተሳሰብ የሚሰፍንበት በመሆኑ የህዝቦች አንድነትን በማፅናቱ ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። በህዝቦች መካከል ኅብረትና ትብብር የሚጠናከሩበት ከዘመን መለወጫነት ባሻገር ድንቅ አሻጋሪ ዕሴቶቻችን ናቸው፡፡
በየአመቱ ባህላዊ ስርዓትና ትውፊታቸውን ጠብቀው የሚከበሩት በዓላቱ፤ ዘንድሮም በተለያዩ ባህለዊ ኩነቶች፣ የአደባባይ ክዋነዎች፣ የህዝቦች አብሮነትንና አንድነትን በሚያፀኑ ስርዓቶች በማንነት ቀለማት አሸብርቀው፤ በኅብረ-ብሔራዊነት ደምቀው እንደየብሔር/ብሔረሰቡ የጊዜ ቀመር በመከበር ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
*መንግሥት ኮሙኒኬሽን፦ እነዚህን የብሔር/ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላትን ለማጠናከር እና ሌሎችም እንዲለሙ ከማድረግ አኳያ ቢሮው ምን እየሰራ ይገኛል?
*አቶ ፋንታሁን፦ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እነዚህ የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ለምተው፣ ተጠብቀውና በተገቢው ተሰንደው በብሔራዊ እና በአለም ቅርስነት መዝገብ መመዝገብ ስላለባቸው በጥናትና ምርምር እንዲደገፉ ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ጥናታዊ ጽሁፎችና የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ወደ ክብረ በዓላት ደረጃ ያልደረሱ የብሔረሰቦች ባህሎች ጎልተው ወደፊት እንዲወጡ እና መከበር የተጀመሩት ተጠናክረው እንዲሄዱ ከማድረግ አኳያ በተደራጀ እና በተቀናጀ መንገድ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ታቅዶ በመሠራት ላይ ነው፡፡
*መንግሥት ኮሙኒኬሽን፦ የብሔር/ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት መከበር የክልሉ ቱሪዝም ዘርፍ ከማነቃቃት አኳያ ያለው ሚና ምንድነው?
*አቶ ፋንታሁን፦ ባህል፣ ታሪክና ተፈጥሮ ለቱሪዝም መሠረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ የብሔር/ብሔረሰቦች ዘመን መለወጫ በዓላት ስከበሩ በየአካባቢው የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ የቱሪዝም ገቢ በማሳደግና በማነቃነቅ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
የክልሉ ህዝቦች የባህል፣ የታሪክ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲጠናከርና ህብረብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት እና የሀገሪቱ የሠላም ዕሴት ግንባታ ላይ የክልላችን ህዝቦች ሚና አጉልቶ ለማውጣት ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ተግባር በመሆኑ ይህንን የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት አከባበር በማጠናከር ለዘላቂ ሠላም አብሮነት እና ብልጽግና ለማዋል የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ለማሳካት ታቅዶ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
*መንግሥት ኮሙኒኬሽን፦ ስለሰጡን ሀሳብና ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን!
*አቶ ፋንታሁን፦ እኔም አመሰግናለሁ!
በተከተል ወ/ሚካኤል
