
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ ለሸኮ ብሔር የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል “ቲካሻ ቤንጊ” የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን አስመልክቶ ባስተለለፉት መልዕክት፣ የሸኮ ብሔር የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ትውፊት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ ለዘመናት የቆዩና ዛሬም ድረስ ለሰላማችን መሠረት የሆኑ ባህላዊ የእርቅና የዳኝነት ሥርዓቶች ባለቤት ነው ያሉት ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ፣ ቲካሻ ቤንጊ ይህንን ታሪካዊ እሴት የሚያስተዋውቅ ትልቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል። በዓሉ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የሸኮ ብሔር ከአያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ታላቅ ሥልጣኔ የሚያሳይበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቲካሻ ቤንጊ ያከናወኑትን ስራ መዝነው፣ ላገኙት ውጤት ፈጣሪን አመስግነው ለቀጣዩ የሥራ ዘመን የሚዘጋጁበት የሥራና የምስጋና በዓል ነውም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም በክልሉ የሚገኙ መሰል ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ከአካባቢ ሁነትነት አልፈው የቱሪዝም መዳረሻ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቲካሻ ቤንጊ እሴቶችንም ለዘላቂ ሠላም ግንባታ ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።
እንደ ቲካሻ ቤንጊ ያሉ በዓላትን ታሪካዊ ዳራቸውን ሳይለቁ በማልማትና በማስተዋወቅ፣ ለክልላችንም ሆነ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ በትኩረት መሥራት ይገባናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ በዓሉ የሠላም፣የፍቅር፣ የአብሮነትና የአንድነት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
