
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ለሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል” ቲካሻ ቤንጊ ” እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቲካሻ ቤንጊ” የሸኮ ህዝብ አዝመራውን ከንፋሰና ከበሽታ ጠብቆ ላቆየው ለፈጣሪያቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት ለዘመናት የዳበረ ድንቅ የባህል እሴት መሆኑ አንስተዋል።
በዚህ ድንቅ ስርዓት ሸኮዎች ከበሽታና ከቸነፈር ተጠብቀው ደስታ ወደሞላበት የአዝመራ ወቅት፣ አዲስ ምዕራፍና አዲስ ዓመት መሻገራቸውን የሚያበስሩበትና ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።
በአዲሱ ዘመን ልጆቻቸውና ሀብታቸው በሰላም እንዲከርሙ፣ የተወለዱት እንዲያድጉ፣ የተዘራው እህል ፍሬ እንድያፈራና አጠቃላይ ምድሪቱ ፣ ደኑ፣ሰማይና አየሩ ሁሉ ሰላም እንዲሆን በመመኘት ፀሎታቸውን ለፈጣሪ ያደርሳሉ ብለዋል።
ቲካሻ ቤንጊ የሀገረሰብ እውቀቶች እና የተደመረ ጥበባትን ያቀናጀ ፣ የስራ ባህልን የሚያበረታታ፣ጤናማ ማህበራዊ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት መልካም እሴቶችን በሀገር በቀል ቅኝት ያቆየ የዘመን መለወጫ በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቲካሻ ቤንጊ ባህላዊ እሴቶች የአብሮነትና አንድነት ትስስር የሚያጠናክሩ፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴቶችን የሚያጎሉ የኅብረ ብሄራዊነት ማሳያ ታላቅ በዓል በመሆኑ ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የብሔረሰቡን ድልብ ማህበራዊ እሴቶችን በመጠቀም አስተማማኝና ዘላቂ አዎንታዊ ሰላም ለመገንባትና ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማደርጀት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም አንስተዋል።
በዓሉ የአብሮነት እና የወደፊት ተስፋ መልዕክት ነው ያሉት አቶ ፍቅሬ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ይህን ድንቅ እሴት በመጠበቅ፣ በማልማትና ፣ በማሳደግ ለትውልድ ለማስተላለፍና ቱሪስትን በመሳብ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የራሳቸውን ባህል ፣ቋንቋ፣ ታሪክ የመጠበቅ፣ የማልማትና የማሳወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥ እና በአደባባይ ወጥተው እንዲያከብሩ ዕድል በመፈጠሩ ዛሬ የሸኮ ብሔረሰብ ለሶስተኛ ጋዜ በዓላቸውን በደመቀ ሁኔታ እያከበሩ መሆኑን አንስተዋል።
ፓርቲያችን ብልጽግና የቀደሙ ባህሎችን ከመጠበቅ ባሻገር ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ አሻራና ቅርስ ሆኖ ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፉ አበክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡
በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ /አደረሰን !
