የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ዘርፍን ለማጠናከር ያለመ ዉይይት በዳዉሮ ዞን ተካሄደ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት በዳዉሮ ዞን የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ በዳውሮ ዞን ተካሂዷል።

በክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በአቶ የሺዋስ ዓለሙ የተመራ የአመራር ቡድን ከዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በየደረጃው የሚገኙ የኮሙኒኬሽን መዋቅሮችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ምክክር አድርጓል።

የሚዲያ ሚና ለልማት ስኬት ወሳኝ ነው አቶ የሺዋስ ዓለሙ ፤ በዞኑ እየተመዘገቡ ያሉ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎችን ለሕዝብ ለማድረስና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማጉላት የሚዲያ ሚና አማራጭ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም የአካባቢውን ድንቅ ባህል፣ ወግና እሴት ለዓለም ለማስተዋወቅ ያሉትን የሚዲያ አማራጮች አሟጥጦ መጠቀም ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ ለተቋሙ መጠናከር ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።ለዚህም በማቴሪያልና በሰዉ ኃይል ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊትገበየሁ በበኩላቸው ፤ በዞኑ የሚገኙ የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ተቋማትን አቅም በመገንባት ረገድ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ተቋማቱ ለበለጠ ተደራሽነትና ውጤታማነት እንዲሰሩም የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የዳውሮ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ መላኩ ተረፈ በበኩላቸው፤ የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ረገድ የሚታየውን ጥረት ጽሕፈት ቤታቸው በቅርበት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

ይህ የጋራ የምክክር መድረክ በዞኑ ያለውን የመረጃ ፍሰት ለማዘመንና በየደረጃው ያሉ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ አዲስ መነቃቃት እንደሚፈጥር ይጠበቃል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *