የሸኮ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የህንጻ ግንባታ የመሠረተ-ድንጋይ ተቀመጠ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት፣በቤንች ሸኮ ዞን በሸኮ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ባለሁለት ወለል ሕንፃ ግንባታ በይፋ ተጀመረ። ለዚህም ግንባታ የመሠረተ-ድንጋይ ያስቀመጡት የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸው።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ ብልፅግና ተቋማዊ ግንባታን አንዱ ግቡ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ ሰሞኑን በካፋ ዞን ብቻ አራት የመሠረተ-ድንጋይ ማስቀመጥ መርሃ ግብሮች መከናወናቸውን እንደ ማሳያ አንስተዋል።

እንደ ሀገር ካስቀመጣቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የተቋም ግንባታ ዋነኛው መሆኑን አቶ ፍቅሬ ገልጸዋል።

የተቋም ግንባታ ፈጣንና ቀልጣፍ አገልግሎት ለመስጠት፣ የዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ፣ ከድህነት ለማላቀቅ እንዲሁም የሀገራችን የብልፅግና ጉዞ ለማሳለጥና ሀገርን በማጽናት ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማረጋገጥ የተቋም ግንባታ አየይተኬ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

በተቋም ግንባታ ተግባራት በብልፅግና ፓርቲ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በውጤታማነት እየተከናወነ ይገኛል ሲሉ ጠቁመዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው፣ የሸኮ ወረዳ ቀደም ሲል ከነበረበት የጸጥታ ችግር ወጥቶ አሁን ለልማት መብቃቱ የፀጥታ ኃይሉና የሕዝቡ የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ፓርቲው በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የራሱ ቢሮ እንዲኖረው እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የከተማዋ ከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳመለከቱት፣ ሸኮ ከተማ ከተመሠረተች ገና አንድ ዓመት ከሰባት ወራት ቢሆናትም፣ ነዋሪውን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። አሁን ለሚገነባው የፓርቲው ጽሕፈት ቤትም ሕዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።ግንባታዉም 75 ሚሊየን ብር ወጪ እንደሚገነባ ተጠቅሷል።

በዕለቱ ለግንባታው ማጠናቀቂያ የሚሆን የቁም ከብትና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የክልሉ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ሲል ቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *