




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በታርጫ ከተማ እያካሄደ ይገኛል። በጉባኤው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ካነሱዋቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፦
1. የአስተዳደርና የሰላም ግንባታ
የአመራር አቅም ግንባታ፦ ለአመራሩ በተለያዩ ዘርፎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን፣ በብልሹ አሰራር የተሳተፉ አመራሮች ላይም ተገቢው እርምጃ ተወስዷል።
የሰላም ሁኔታ፦ በአርሶ አደርና አርብቶ አደር አካባቢዎች ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን በመፍታት አካባቢውን ወደ ሰላማዊ ቀጠና መቀየር ተችሏል።
2. የማህበራዊና የመሰረተ ልማት ስኬቶች
ትምህርት፦ በትምህርት ተደራሽነት ረገድ በክብርት ቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ድጋፍ የተገነባው የቱልጊት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ መጀመሩ ተገልጿል።
ተቋማዊ ግንባታ፦ በ5.7 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነቡ ያሉ የክልል ተቋማት የህንጻ ግንባታ በታቀደላቸው ፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ልማትና ቱሪዝም፦ የመሶብ 1 ማዕከል አገልግሎት መጀመር፣ የ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት አካል የሆነው የደንቢ ኢኮ ሎጅ መመረቅ እንዲሁም የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማቶች ጉልህ ስኬቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
3. የዲጂታል ቴክኖሎጂና የፋይናንስ አፈፃፀም
ዲጂታል ኢትዮጵያ፦ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባና የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ዕዳ ክፍያ፦ ክልሉ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ዕዳ መመለስ መቻሉ ተመላክቷል።
ርዕሰ መስተዳድ የ2018 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
