ሴቶች ለሀገር ግንባታና ለብልጽግና ጉዞ ያላቸው ሚና የማይተካ ነው ፦አቶ አለማየሁ አለሙ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አስተባባሪነት ክልላዊ የንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ በቴፒ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩ “በሴቶች ተሳትፎ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በየደረጃው ከሚገኙ ሴቶች ጋር በተካሄዱ የንቅናቄ ሥራዎች ላይ ግምገማ ለማድረግና ለቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ለመወሰን የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሸካ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አለሙ እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ የሴቶችን ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድ ብዙ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ሴቶች በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑን አስገንዝበዋል።

​ በጉዞው ላይ የሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ “ትርክቶች” እና እንቅፋቶች ሳይበግሩን፣ አንድ የሚያደርገንን የኢትዮጵያዊነት እሴት በማጽናት ወደፊት መጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

​በቀጣይ የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

​በሴቶች መካከል ያለውን የእህትማማችነት እና የወንድማማችነት ግንኙነት በማጠናከር ለሀገር ብልጽግና በጋራ መቆም እንደሚገባም አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ትዕግስት ተረፈ በበኩላቸው ሴቶች በፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጪነት፣ በማኅበራዊ ግንኙነቶችና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

​ ሴቶች ያገኙትን ዕድል በመጠቀም ለሀገራቸው ሰላም፣ ለአንድነትና ለብልጽግና ጉዞ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል ኢንጅነር ትዕግስት።

የሸካ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወ/ሮ አካልነሽ አየነው በበኩላቸው፣ ፓርቲው የሴቶችን ሚና በማረጋገጥ በሁሉም ዘርፎች የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በንቅናቄው ሂደት ከቀበሌ ጀምሮ በ59 ቀበሌዎች የሚገኙ ከ47 ሺህ በላይ ሴቶችን በማሳተፍ ሰፊ የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸው አመላክተዋል ።

በመድረኩ ላይ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፣ የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙ፣ በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ኢንጅነር ትዕግስት ተረፈ እንዲሁም ከክልል፣ ከዞን፣ ከከተማና ከወረዳ የተውጣጡ ሴት አመራሮችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *