




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ያላቸውን ሚና በተመለከተ ከክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከቢሮአችን ጋር ቆይታ ካደረጉት መካከል ብልፅግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ፣ ሠላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኙበታል።
ፓርቲዎቹ ምርጫው በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅና የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበት እንዲሆን በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በባለፉት ምርጫዎች የታዩ ክፍተቶች እንዳይደገሙ ፓርቲዎቹ ለአባላቶቻቸው፣ ለዕጩዎቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ሰፊ ስልጠና እየሰጡ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በዚህም በተለይም በምርጫ ሕግጋት፣ ደንቦችና የሥነ-ምግባር መመሪያዎች፤በመራጮችና ዕጩዎች መብትና ግዴታ፤
ብሔርን፣ ሃይማኖትንና ጾታን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮችን በመከላከል ዙሪያ እንደሆነ ጠቁሟል።
ፓርቲዎቹ በማኅበራዊ ሚዲያ ሀገርን የሚያፈርሱና ሕዝብን የሚያጋጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን እንደሚቆጣጠሩም አረጋግጠዋል።
ከዚህም ባለፈ፣ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ችግር በሚፈጥሩ አመራሮችና አባላት ላይ ተገቢው የፖለቲካ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
የሰላማዊ ትግል ብቸኛው መሣሪያ የመራጭነት ካርድ መሆኑን የገለጹት ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የትጥቅ ትግል አማራጭ ሊሆን እንደማይችልም አሳስበዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በሙሉ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት የትኛው ፓርቲ ለሀገር የተሻለ እንደሚሠራ በሰከነ መንፈስ እንዲያመዛዝኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ምርጫው ከቅስቀሳ ጀምሮ እስከ ውጤት ማስታወቂያ ድረስ ስኬታማ እንዲሆን ከምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ከጸጥታ አካላትና ከየደረጃው ከሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር በቅንጅት እየሰሩ ስለመገኘታቸውንም አመልክተዋል።
በፍቅር ከበደ
