




በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በተገኙበት በቦንጋ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤቱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት የማስተባበሪያው ስራ እንዲጀመር አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ መከፈት የሚዲያ ተደራሽነትን እንደሚያሰፋ ጠቅሰው፤ በተለይም ከዚህ ቀደም የቀጥታ ስርጭት ለማካሄድ ከሃዋሳ ሚደረግ የወጪና የሰው ኃይል ጫናን እንደሚቀንስ ገልጸዋል።
ድርጅቱ የብዝሃነት ድምፅ መሆኑን በመጠቆም ለአራቱ ክልሎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ የሚያገለግል መሆኑን አመልክተው፤ የክልሉ መረጃ በቅርበት እንዲደርስ የነበንን ጥያቄ መመልስ እንደሚችልም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ምህዳር ማስፋት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግስት ማስተባበሪያው ዓላማውን እንዲያሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ገነሞ ድርጅቱ የብዝሃነት ድምፅ መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ የሚካሄዱ የልማት ስራዎች፣ የመልካም አስተዳደር ክንውኖች እና ወቅታዊ ጉዳዮች በቀጥታ ስርጭት ለህዝብ ማድረግ የሚያስችል እስቱዲዮ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ከአራቱ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች የሚዘጋጁ የይዘት ሥራዎች በጥራት እና በተደራሽነት እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ለስራው ውጤታማነት ከቅርንጫፍ ጣቢያዎች በውድድር የተመረጡ ባለሙያዎች መመደባቸውንና አስፈላጊ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ለማስተባበሪያው መቋቋም የክልሉ መንግስት ያደረገውን ድጋፍ አመስግነዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት እና የአራቱ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ሥራ አስኪያጆች ተገኝተዋል።
በበረከት ኢዮብ
