




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ ማጭበርበር ወንጀልን ለመዋጋትና የህግ ማስከበር ስራን ለማጠናከር ያለመ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የክልሉን የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ለማጠናከርና የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከል የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ተሳታፊዎቹ አክለውም ደረሰኝ በማበላለጥ፣ ደረሰኝ ባለመቁረጥና በተለያዩ መንገዶች የታክስ ስወራ በሚፈጽሙ የንግድ ተቋማት ላይ ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የታክስ ስወራን በዘላቂነት ለመከላከል በማጭበርበር ተግባር ላይ ለሚሰማሩ አካላት ከአስተዳደራዊ እርምጃ ባለፈ፣ ተመጣጣኝና አስተማሪ የህግ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚገባም በመድረኩ ላይ ሃሳብ አቅርበዋል።
የታክስ ማጭበርበር ወንጀል መዋጋትና የህግ ማስከበር ስራን ማጠናከር እንዲያስችል በየደረጃው ድጋፍና ክትትል ማጠናከር፣ ችግሮች ሲከሰቱ ጥቆማ መስጠት እንዲሁም ፍትህ ተቋማት በታክስ ማጭበርበር ለተያዙ መዝገቦች ፈጣኝ ምላሽ መስጠት አለባቸው ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል እንዲያዳብር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አንስተዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የህግ ማስከበር ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት በላይ በበኩላቸው፣በክልሉ ከፍተኛው የገቢ ምንጭ የሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።
የክልሉን የልማት ወጪ በገቢ ለመሸፈን ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንጂቻል የግብር/ታክስ ህግ ልዕልና እንዲረጋገጥ በአበክሮ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው ኃላፊዋ ያብራሩት።
የደረሠኝ ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም ሀሰተኛ የደረሰኝ ህትመት ላይ በየደረጃው ባሉት መዋቅሮች ላይ የተቀናጀ ፍተሻ ማድረግና እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።
ማሕበረሰቡ በግብይት ወቅት ሂሳብ ከመክፈሉ በፊት ደረሰኝ የመጠየቅና የማየት መብትና ግዴታ እንዲሁም ነጋዴውም ደረሰኝ የመቁረጥ ግዴታውን እንዲወጣም ወ/ሮ ትዕግስት በላይ አሳስበዋል።
በማከልም በክልሉ በታክስ ማጭበርበር የተያዙ መዝገቦች ፈጣን እልባት እንዲያገኙ በየደረጃው የሚገኙ ፍትህ ተቋማት ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
በፍቅር ከበደ
