የመጋቢት 24 ትሩፋት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል
የህዝቦች የዘመናት በፍትሃዊነት የመልማትና የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች በሰላማዊ እና በህገ-መንግስታዊ መንገድ በለውጡ መንግስት ምላሽ በማግኘታቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ህዳር 14/2014 ዓ.ም ተመስርቷል። በመደመር ዕሳቤ የሚመራው መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ግልጽ ራዕይና ስትራቴጂ ነድፎ ሲንቀሳቀስ የቆየ በመሆኑ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውስጥ በርካታ የልማት ድሎች ተመዝግበዋል፡፡ ክልሉ እጅግ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ የተለያዩ ብሔር/ብሔረሰቦች ባህልና ዕምቅ የኢኮኖሚ አቅም ያለው በመሆኑ፣ እነዚህን ፀጋዎች ወደ ተጨባጭ ልማት ለመቀየር ባለፉት ዓመታት የተቀናጀ ጥረት ተደርጓል።



















የፖለቲካ እና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች
የክልሉ ምስረታ ራሱ ትልቁ የፖለቲካ ስኬት ሲሆን፣ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ላይ በቀጥታ የመወሰን መብቱን በተግባር ተጠቅሞበታል። ይህም በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ውስጥ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተሟላ መልኩ እንዲከበር አስችሏል። የክልሉ ህዝብ በመደመር ዕሳቤ በሚመራው መንግስት አማካይነት በተጎናፀፈው የፖለቲካ መብት የራሱን ህገ-መንግስት፣ ሰንደቅዓላማና አርማ በመቅረፅ እንዲሁም የክልል ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤትን አቋቁሞ የተለያዩ አዋጆችንና የአሰራር ማዕቀፎችን በራሱ ምክር ቤት አቅርቦ በማጸደቅ እየሠራ ይገኛል፡፡
የመልካም አስተዳደር ዕሴቶችን ለማስፈን እና የህዝብን ቅሬታዎች ለመፍታት የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዓቶች ተዘርግተዋል። በዚህም ቀደምሲል ከርቀት አንፃር ህዝቡ ሲያማርር የነበረውን መንግስታዊ አገልግሎት የተደራሽነት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት መጀመሩ በክልላችን ከታዩ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች አንዱ ነው፡፡




ከዚህም በተጨማሪ ክልል በመሆናችን ክቡር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮች፣ ርዕሳነ-መስተዳድሮችና አምባሳደሮች በተከታታይ ክልሉን በመጎብኘት ያሉብንን የመልማት ችግሮቻችንን በዓይናቸው በማየት ለመፍትሄው የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በተከናወኑ ስራዎች፣ ቀደም ሲል በአንዳንድ የክልላችን አካባቢዎች በተደጋጋሚ ይስተዋሉ የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ምክንያት የተፈጠሩ የዜጎች ሞት፣ የአካል መጉደል፣ መፈናቀል፣ ንብረት መውደም፣ ዘረፋና ተያያዥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን በባህላዊ ሥርዓት እና በህግ የበላይነት እንዲፈቱ ተደርጓል። በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅሮቻችን ከህዝቡና ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ችግሮችን በመፍታት አንጻራዊ ሠላም እንዲሰፍን አድርገናል፡፡ ይህም ለልማት ስራዎች መፋጠን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። የክልሉ የፀጥታ መዋቅር በሰው ኃይል እና በቁሳቁስ እንዲጠናከር መደረጉ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር እምነት የሚጥል አስተማማኝ ከባቢ መፍጠር ተችሏል። የፍትህ አካላትን አቅም በመገንባት ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ዜጎች ፈጣን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የፍትህ ተደራሽነትም ከምንጊዜውም በላይ ሰፍቷል።
የኢኮኖሚ ዘርፍ ውጤቶች
የመደመር መንግስትን ብዝሃ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ፖሊሲን (የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድን፣ የቱሪዝምና የቴክኖሎጂ ዘርፎች) በሚገባ በመተግበር ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ባለፉት አመታት ተመዝግበዋል፡፡ ክልሉ እምቅ የግብርና አቅም ያለው በመሆኑ ለግብርናው ዘመናዊነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። በኩታ ገጠም የግብርና አሰራር እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በርካታ ተጀምረው የቀሩ የመስኖ አውታሮች ግንባታ በማስቀጠልና በማጠናቀቅ በዝናብ ጥገኛ የነበረው የክልላችንን አስተራረስ ባህል በመቀየር በዓመት ሶስት ዙር የማረስ ልምድን እያጎለበትን እንገኛለን፡፡ በዚህም በክልላችን የማይታወቀውን የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሩዝና ሌሎች ምርቶችን በማስፋትና በባህላዊ አስተራረስ ዘዴ ላይ የቆየውን እርሻ መካናይዝድ ማድረግ በመጀመራችን የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር አልፎ ምርትና ምርታማነት እያደገ ይገኛል፡፡





ክልሉ የቡና፣ የቅመማ ቅመም እና የፍራፍሬ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ምርቶች ለውጭ ገበያ እና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በከፍተኛ ጥራትና መጠን ለማቅረብ የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት አስመዝግበዋል። የመደመር መንግስት የሚከተለውን የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ መርህን ተከትለን በመሥራታችን በእነዚህ ምርቶች የተሻለ ውጤት እያስመዘገብን እንገኛለን፡፡ በተለይ ቡናን በማምረትና ለሀገር አቀፍና ውጪ ገበያ በማቅረብ ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ አንገኛለን፡፡ የተለያዩ የቅመማቅመም ምርቶች እንደ ኮረሪማ፣ ጥሚዝ፣ ዝንጅብል፣ ቁንዶበርበሬ፣ እርድ እና የመሳሰሉት በክልሉ በስፋት ተመርተው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረቡ የሚገኙ ሲሆን ከፍራፍሬም አንጻር እንደ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ አናናስ ያሉ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚመረቱ ሲሆን ለብዝሃ ግብርና ምርት በተሰጠው ልዩ ትኩረት በሀገሪቱ ገበያም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር አማካኝነት በክልሉ የወተት፣ የስጋ፣ የዶሮ እና የማር ምርትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ ትርፍ ምርት እንዲፈጠር አድርገዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን መሰረት በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህም የክልሉን የደን ሽፋን ከመጠበቅ ባለፈ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ አበርክቶ ያላቸው እንደ ፍራፍሬ ያሉ በስፋት ተተክለው ውጤት ማሳየት ጀምረዋል፡፡


ገቢን በተመለከተ ክልሉ ሲመሠረት ከሁለት ቢሊዮን ብር ባላይ ከማይሰበሰብበት በርካታ አሳሪ ህጎችን በማሻሻልና የገቢ ምንጮችን በማሳደግ በየአመቱ እያደገ መጥቶ በ2018 የበጀት ዓመት 18 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እስካሁን ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም የክልሉን የልማት ፍላጎት እያገዘ ይገኛል፡፡
በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመሳብ ምቹ የሆኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የማበረታቻ ስርዓቶች የተዘረጉ ሲሆን፣ በርካታ ባለሀብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ ተደርጓል። ክልላችንም በማዕድን ሀብቱ የታወቀ ቢሆንም ቀደም ሲል ለዘርፉ ከተሰጠው አነስተኛ ትኩረት የተነሳ ወርቅ በባህላዊ ዜዴ ሲመረት ቆይቷል፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ማዕድን ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የብዝሃ-ኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ወርቅን በዘመናዊ መንገድ ለማምረት ዘመናዊ ማሽኖችን የመጠቀም እንቅስቃሴ በሰፊው ተጀምሯል፡፡ ከወርቅ በተጨማሪ የድንጋይ ከሰል ክምችት በክልላችን ከፍተኛ በመሆኑ የሀገራችንን 25 በመቶ የከሰል ድንጋይ ፍላጎትን የሚያረካና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬን የሚያስቀር የድንጋይ ከሰል ፋብርካ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ተገንብቶ ሥራ ጀምሯል፡፡ ይህም የማዕድን ዘርፉን ከማዘመን በላይ ለአከባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡
በተለይ የክልሉን የቱሪዝም እምቅ አቅም በተገቢው የተረዳው የመደመር መንግስት በሰጠን ዕድል በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በገበታ መርሃ ግብር ከተገነቡ ፕሮጀክቶች መካከል የሀላላ ኬላ ሪዞርትና የጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ እንዲሁም በደንቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ አከባቢ የተገነባው የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የደንቢ ኢኪ ሎጅ፣ የሚዛን-አማን አለምዓቀፍ እና የቦንጋ መለስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት ሳቢ ልማቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ትልቁ ለሀገርቱ የኤልክትሪክ ኃይል አቅራቢ የግቤ ሶስትና አራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የሚገኙት በዚህ ክልል ውስጥ በመሆኑ ይህም ከኤሌክትሪክ ማመንጨት በተጨማሪ ለክልላችን ትልቅ የቱሪዝም አቅም ይሆናሉ፡፡ በዚህም በክልላችን ከፍተኛ የቱሪዝም መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡


የማህበራዊ ዘርፍ ልማት ውጤቶች
በማህበራዊ ዘርፍ፣ በተለይም በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ርምጃዎች ተወስደዋል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታና የነባሮቹ ደረጃ ማሻሻል በስፋት ተከናውኗል። የህፃናት ማቆያ እና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የተሰሩ ስራዎች ለህፃናት የተሻለ መሰረት ለመጣል ረድተዋል። ይህም ህፃናት ወደ መደበኛ ትምህርት ሲገቡ ዝግጁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ እና ውጤታማነት ለማሳደግ ልዩ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲቆዩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች በየደረጃው ተፈጥረዋል።
በጤናው ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የጤና ተቋማት ግንባታ ተካሂዷል። ባለፉት አራት አመታት ብቻ ተጀምረው የቆሙ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች (የአዲዮ ካካ፣ የማሻ፣ የቆንዳና የዋካ ሆስፒታሎች) ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም የጤና ጣቢያዎችና የጤና ኬላዎች ተደራሽነት ለማሳደግ በተሠሩ ሥራዎች የእናቶች እና የህፃናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል። የህብረተሰብ አቀፍ ጤና መድህን (CBHI) አሰራርን በክልሉ በስፋት ተግባራዊ በማድረግ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ያለ ኢኮኖሚ ችግር የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።
ክልላችን 13 ነባር ብሔር/ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያሉበት በመሆኑ የክልሉን ህዝቦች አንድነትና ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩና የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ግንባታን የሚያሳልጡ ተግባራትም እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ብሔር/ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቱባ ባህሎችንና ዕሰቶችን ቱባ ባህል፣ ቋንቋ፣ ዕሴት እና ታሪክ ለመጠበቅና ለማበልፀግ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በየዓመቱ የሚከበሩ የብሔር/ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓላት ህዝቦችን አንድነትና ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትን ከማጠናከር ባለፈ የቱሪዝም መስህብ እየሆኑ መጥተዋል፡፡



የመሠረተ ልማት ግንባታ ውጤቶች
ቀደም ሲል ተጀምረው ያልጠጠናወቁ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ትኩረት ሰጥቶ በማጠናቀቅና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በፍጥነት በማጠናቀቅ የክልሉን የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከነበረበት 32 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ግንባታቸው ተጀምሮ የቆሙ በርካታ የመስኖ አውታሮች እና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም በክልሉ መንግስት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ግንባታቸው እንደገና ቀጥለውና ተጠናቀው አገልግሎት መሥጠት ጀምረዋል፡፡





የመንገድ መሠረተ-ልማትን በተመለከተም በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተጀምረው ግንባታቸው የተቋረጠ የአስፓልት መንገዶች (የሚዛን-ቴፒ፣ የጅማ-ጪዳ-ታርጫ፣ የጎሬ-ማሻ-ቴፒ፣ የቴፒ ሽሽንዳ፣ የወልደሃኔ-ዱርጊ እና የዲሪ-ማሻ) መንገዶች ፕሮጀክቶች አሁንም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ችግሮች ቢኖሩም የተቋረጠውን ግንባታ እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን በሶስቱም ዲስትሪክቶች (ሚዛን፣ ቦንጋና ታርጫ) እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ በርካታ የገጠር መንገዶች ጥገና እንዲሁም አዳድስ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ የከተማ ልማትን በተመለከተ በኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ በቦንጋ፣ በሚዛን-አማን፣ በታርጫ፣ በአመያ፣ በቴፒና ሌሎች ከተሞች እየተሠሩ ያሉ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ መዝናኛ ፓርኮች ከተሞችን ውብ ከማድረግም ባለፈ ለዜጎች ምቹና ተስማሚ መኖሪያ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
