






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቴፒ ከተማ ሲያካሂድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቀቀ።
በመድረኩ በዘጠኝ ወራት የተመዘገቡ የተሻለ አፈጻጸሞችን ማጠናከር እና ጉድለቶችን ማረም የሚያስችሉ ገንቢ ሀሳቦች ተነስተው የጋራ ውይይት ተደርጓል።
በግምገማው ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን አመራሩ የፓርቲውን መደበኛና ኢንሼቲቭ ሥራዎች በላቀ ቁርጠኝነት መምራትና በተግባር መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም የፓርቲው ቁልፍ ኢንሼቲቮች የሆኑት ተረጂነት መቀነስ፣ የኑሮ ውድነት ማቃለል፣ የገጠር ሞዴል መንደር፣ የሌማት ትሩፋት እና ኮሪደር ልማት በፍጥነትና በጥራት እንዲፈጸሙ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አመራሩና አባሉ ሀገራዊ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ሥጋቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ሀገሩንና ክልሉን ማሻገር ይጠበቅበታልም ብለዋል።
የየአካባቢ ነባራዊ ሁኔታ አዝማሚያዎችን በመገምገምና በመተንተን በየማህበራዊ መሠረቶች ሰነድ በማዘጋጀት የውይይት በማካሄድ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይገባልም ብለዋል አቶ ፍቅሬ አማን።
የአመራሩና የአባላት የተግባር፣ አመለካከትና አስተሳሰብ አንድነት ለመፍጠር የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉም እንዲሁ።
የፓርቲውን ውጤቶችና ትሩፋቶች ለህዝብ በትክክል ለማስተዋወቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች በትኩረት መከናወን እንዳለባቸው ነው አቶ ፍቅሬ አማን ያሳሰቡት።
ፓርቲው በምርጫ አብላጫ ድል እንዲቀዳጅ አመራሩና አባሉ ሚናቸውን በተገቢው እንዲወጡ አቶ ፍቅሬ አማን አስገንዝበዋል።
ፓርቲዉ በየጊዜው ከሕዝቡ ጋር የሚያካሂዳቸው ውይይቶች የልማት ሥራዎችን በቅንጅት ለመፈጸም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል ያሉት ደግሞ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ ናቸዉ።
በክልሉ ተግባራትን በቅንጅት የመፈጸም፣ የመደጋገፍና የመተባበር ባህል እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ነጋ የዓመቱ ሥራ በተሻለ ሁኔታ እንዲፈጸም በቀሪ ወራት ቀሪ ሥራዎችን ቆጥሮ ማከናወን ይገባልም ብለዋል።
ለፓርቲ ሥራዎች ውጤታማነት የአመራርና አባላት ምዘናና ግምገማ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ ናቸው።
የተጀመሩ የሕዝቡ የልማት ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱና የምርጫ ስራው የተሳካ እንዲሆን በየደረጃው አደረጃጀቶችን መፈተሽና ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ በላይ ተሰማ።
በፍቅር ከበደ
