ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እያሳየች ያለችው የላቀ ውጤትና እመርታ ተጠናክሮ ይቀጥላል

Spread the love

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እያሳየች ያለችው የላቀ ውጤትና እመርታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቲ ኮሚቴ ገለፀ።

በአየር መንገዱ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰነዘሩ አሉባልታዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ከእውነታ የራቁና ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑም ተጠቁሟል።

በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩ በጥብቅ ዲሲፕሊንና አሠራር የሚስተካከሉ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሀገር ከፍታና የመልካም ገጽታ ማሳያነት የሚያስቀጥሉ ዘመናዊ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

በአየር መንገዱ የሀገር ከፍታና የመልካም ገጽታ ማሳያነትን የሚያስቀጥሉ ዘመናዊ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቲ ኮሚቴ ገለጸ።

በዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የላቀ ስምና ዝና ካላቸው አየር መንገዶች አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘመናዊ አሠራሩ፣ በተቀላጠፈ መስተንግዶና በሌሎችም ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን አሠራሮች በየጊዜው ተሸላሚ እየሆነ እስከ አሁንም ቀጥሏል።

የአየር መንገዱን ዘመናዊነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ዘመናዊ አሠራሮችና የሪፎርም ሥራዎች በመተግበራቸው በስኬታማነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በአየር መንገዱ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቲ ኮሚቴ በግምገማው በማሳያዎች ጭምር ስኬታማነቱን አረጋግጧል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የላቀ ውጤትና እመርታ ያሳየች መሆኑን ገልጸው፤ ይኸው ሥራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር መንገዱን የሀገር ከፍታ ማሳያና የመልካም ገፅታ መገለጫነት የሚያስቀጥሉ አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮች አሁንም ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት የሀገር ኩራትና የኢትዮጵያውያን ምልክት ከመሆንም ባለፈ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዘርፍ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የአየር መንገዱን ስምና ዝና ጠብቆ ስኬታማነቱን ማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።

የአየር መንገዱ ስኬታማ ጉዞ አሁንም በላቀ መልኩ መቀጠሉን የተናገሩት ዶክተር ዓለሙ፤ በተቃራኒው መልካም ስሙን ለማጠልሸት የሚጥሩ አካላት እንዳሉም ጠቁመዋል።

በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በጥብቅ ዲሲፕሊንና አሠራር የሚስተካከሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአየር መንገዱ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰነዘሩ አሉባልታዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ግን ከእውነታ የራቁና በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየትኛውም ያልተገባ ዘመቻ ሳይደናገር ከሀገር ኩራትነቱ ባለፈ በዓለም ተመራጭ አየር መንገድነቱ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ በሁሉም ዘርፎች በፈጣን እድገትና ውጤታማነት መቀጠሉን ገልፀዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት መንገደኞችን በማጓጓዝ ረገድ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ፣ በገቢ የ14 በመቶ እንዲሁም ትርፋማነት 22 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ 145 አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቅርቡ የአዳዲስ አውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዝ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በመሆኑም አየር መንገዱ በስኬታማነቱ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በዘመናዊና አዳዲስ አሠራሮች ታግዞ በላቀ ስኬትና ውጤታማነት ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

አየር መንገዱ በአሠራሮች በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በአሠራር ሂደት ችግሮች ካጋጠሙ በፍጥነት የሚፈቱና ምላሽም የሚሰጥባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ፤ የአየር መንገዱ ሰላምና ደኅንነት በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኤርፖርት ዙሪያ የወንጀል ተግባራት ላይ በሚሳተፉ ሰዎች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፤ በኢትዮጵያ የበረራ ድኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ባደረጉት የኦዲት ሪፖርት መረጋገጡን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *