



በምርምርና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ ብልፅግና እውን መሆን ፋይዳው የላቀ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
“መረጃ ለልህቀት፣ የፖሊሲ ሚና ለበለፀገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ቀን መድረክ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ቀረጻ ለሀገር ብልፅግና ያለውን ወሳኝ ሚና አፅንዖት ሰጥተውታል።
ስኬታማ ሀገራት በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን በዕውቀት፣ በምርምርና በስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ ላይ እንደሚተጉ ገልጸዋል።
ፖሊሲ የሁለንተናዊ ሀገራዊ ጉዞ ፋና መሆኑን ጠቅሰው፤ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በዕውቀትና በተግባር መካከል እንደ ድልድይ በመሆን የሀገራዊ ልማት “ድምፅ አልባ ሞተር” ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሽግግር ላይ እንደምትገኝ ገልጸውም፣ በፖሊሲ ጥናትና ቀረፃ ላይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አንኳር ጉዳዮችንም ጠቅሰዋል።
እነዚህም የአየር ንብረት ለውጥና የአረንጓዴ ልማት ጉዳዮች፣ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደርና መዋቅራዊ ሽግግር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የግብርና ምርቶችን ወደ ንግድ ማሸጋገር፣ ቀጣናዊ ትሥሥርና ዓለም አቀፍ የንግድ ተጽዕኖዎች ናቸው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት፤ ፖሊሲ የዜጎችን ሕይወት የሚቀርጽ ተግባራዊ መሣሪያ ሲሆን፤ ዕድሎች እንዴት እንደሚፈጠሩ የሚወስነው ፖሊሲ ነው።
በመንግሥት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በግል ዘርፍና በሲቪክ ማኅበራት መካከል ጠንካራ ትብብር እንዲኖር የጠየቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመደመር መንግሥት ለሀሳብና ለዕሳቤ ልዩ ቦታ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሕዝብና የመንግሥትን መተማመን የሚገነባ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግልም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ቀጣይነት ባለው የዕውቀት ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበትም ነው ያሉት።
በፖሊሲ አማካሪዎች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በግል ዘርፍና በሲቪክ ማኅበራት መካከል ጥራት ላላቸው ፖሊሲዎች ጠንካራ ትብብር እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
