በዳውሮ ዞን የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች እንዲሁም የምርጫ ሂደት ያለበት ደረጃ መገምገሙ ተገለጸ

Spread the love

በዳውሮ ዞን የተከናወኑ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች እንዲሁም የምርጫ ዝግጅት ያለበት ደረጃ በከፍተኛ አመራሮችና በየደረጃው በሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች በዝርዝር ተገምግሟል።

በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በዞኑ የተጀመሩ የመንግስት እና የፓርቲ ሥራዎች ስኬታማ መሆን የሚያስችል ስራ መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግሥትና የፓርቲ አደረጃጀቶች በቅንጅትና በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ አንድነት ሁሉም አስፈጻሚ አካላት የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ ስትራቴጂካዊ የልማት ሥራዎች ለምርጫው ሂደት መሳካት ትልቅ አቅም መሆናቸውን በመጠቆም የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሳይስተጓገሉ በተቀመጠላቸው ጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ የዞኑ አመራር ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሳስበዋል።

አቶ ዳዊት የምርጫ ጣቢያዎች ደህንነት እንዲጠበቅ ፖሊስና ሚሊሻን በመመደብ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ታማኝ እንዲሆን በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የዳውሮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ተረፈ በአጠቃላይ በዞኑ በመንግሥትና በፓርቲ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን የሥራ ሪፖርት አቅርበዋል።

መጪው አገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች በአካባቢው የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች እንዲሁም የልማት ትሩፋቶችን ለማስቀጠል ኅብረተሰቡን በስፋት በማንቀሳቀስ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ቃል ገብተዋል።

በማጠቃለያው የተካሄደው የግምገማ መድረክ በዞኑ ያሉትን የልማት ክፍተቶች ለመሙላትና የሕዝብን የቆዩ ጥያቄዎች ለመመለስ የአመራሩ ዝግጁነት መኖር እንዳለበት አመላክተዋል።

የምርጫ ሥራዎችንና ወቅታዊ የልማት ተግባራትን በማቀናጀት የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቀጣይ በትኩረት የሚሠራበት ዋና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ መሆን እንደሚገባውም ተገልጿል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *