



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በቴፒ ከተማ ለሚገኙ ወጣቶች የህይወት ክህሎት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
የሸካ ዞን ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ከበደ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት በህይወት ክህሎት ዙሪያ ለታዳጊ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ለስብዕና ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቴፒ ከተማ ምክትል ከንቲባና የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደመላሽ ገዳ በበኩላቸው ለወጣቶች የህይወት ክህሎትና ስብዕና ግንባታ ስልጠና መስጠት ለቀጣይ ተተኪና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ሚናው የጎላ ነው ሲሉ አንስተዋል።
አቶ ደመላሽ አክለውም በዚህና መሠል ዘርፎች ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ራሄል ሌዊ በበኩላቸው ከክልላችን ህዝብ ቁጥር ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ጠቁመው እነዚህን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶች የህይወት ክህሎት እና የስብዕና ግንባታ ስልጠና በመስጠት ሀገር ተረካቢና ተተኪ ትውልድ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ የተጀመረው የህይወት ክህሎት ስልጠና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ወ/ሮ ራሄል ሌዊ ጠቁመዋል ።
የቢሮው የወጣቶች ስብዕና ልማት ሥራዎች ዳይሬክቶረት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ተሾመ በወጣቶች የህይወት ክህሎት ዙሪያ የተዘጋጀውን የስልጠና ሰነድ እያቀረቡ ይገኛል።
