



የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እንደሀገር እየታየ ያለዉን የስራ አጥነት ቁጥር በመቀነስ በኢኮኖሚው ዘርፍ የበኩሉን መወጣት የሚችል ትዉልድ የመቅረጽ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አሳሰበ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከካፋ ዞን ስራ፣ ክህሎት፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ መምሪያ ጋር በመተባበር በአዲሱ ዘረመል እሳቤዎች ላይ ያተኮር ስልጠና በዞኑ ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰጥቷል።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ቤቴለሄም ዳንኤል እንደሀገር የዕለት ጉርስ ላይ ያተኮረውን የስራ እድል ፈጠራ አስተሳሰብ በመቀየር ዘላቂ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ አስተሳሰቦችን ማስረጽ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም በሚፈጠሩ ስራዎች ላይ የሠራተኞች ደህነትና ጤንነት ማስጠበቅ ትኩረት የሚሻዉ ጉዳይ በመሆኑ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ስልጠናውን የሰጡት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ አዝመራ ከበደ አሁን ላይ እንደሀገር ችግር ሆኖ የሚታየዉን የዜጎችን የበልቶ ማደር ጥያቄ በመመለስ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል የስራ ዕድል ለመፍጠር የሙያ ተቋማት የተቀናጀ ተግባር ማከናወን ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ ስልጠናም የክህሎት መር ስራዎች ላይ ማተኮር የሚያስችል ግንዛቤ ለዘርፉ ተዋናዮች ለማስገንዘብ ያለመ ነዉ ብለዋል።
የካፋ ዞን ስራ፣ ክህሎት፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ኃይሌ በበኩላቸው፤ ስልጠናዉ በአዲስ መልክ የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎችን ክህሎት መር በማድረግ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ስራዎችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ከገበያ ትስስር ጀምሮ በአግባቡ ለመምራት ታስቦ በዞኑ ጋባዥነት ስልጠናው መሰጠቱንም አብራርተዋል።
በስራ ዕድል ፈጠራ የተቀመጡ ዘረመሎችን በመጠቀም ክልሉ ያለዉን ጸጋ ታሳቢ ባደረግ መልኩ ክህሎት መር ስራዎችን በመፍጠር የዜጎችን የስራ ዕድል ጥያቄ መልስ ለመስጠት መስራት እንደሚገባ በክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አየለ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የሚፈጠሩ ስራዎች በአግባቡ ክትትል የማይደረግባቸው መሆኑ በዘርፉ የተጠበቀውን ያህል ዉጤት እንዳይመዘገብ ማነቆ መሆኑን ተናግረዉ፤ የአሁኑ ስልጠና መሰል ችግሮችን የሚፈታ ነዉ ብለዋል።
የደ.ሬ.ቴ.ድ ቦንጋ ቅርንጫፍ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ በስልጠናው ከተሳተፉት መካከል የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ዲን አቶ ዘላለም ዘዉዴ እና የበለስ ፓራዳይዝ ኮሌጅ ዲን ጥላሁን አጣነዉ ስልጠናው በተቋሙ ዉስጥ የሚታየዉን ክፍተት በመሙላት ገበያ መር ስራዎችን እንዲያከናውን የሚጠቅም ነዉ ብለዋል።
