የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል – የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር::

Spread the love

በክልሎችና በከተሞች የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ ገለጹ።

በአቶ ዳንኤል ተሬሳ የተመራ የሚኒስቴሩ የባለሙያዎች ቡድን በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተሰሩ ሥራዎችን ተዘዋውሮ እየተመለከተ ይገኛል።

ቡድኑ በዛሬው ዕለት ከድሬዳዋ የሥራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊና አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

የቡድኑ ምልከታ በከተሞችና በክልሎች በሥራ ፈጠራና ክህሎት ዘርፍ ለተሰሩ ሥራዎች የሚደረገውን ድጋፍና ክትትል በማጠናከር የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

አቶ ዳንኤል ተሬሳ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ የዜጎችን በተለይም የወጣቶችን የሥራ ዕድል ጥያቄዎች ለመመለስ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንና በዚህም አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ በተቀናጀ መንገድ የሚከናወኑ ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የመንግስት አመራሮች በየጊዜው ወደ ክልሎችና ከተሞች በመሄድ ድጋፋዊ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በክልልና በከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶችን ቁጥር ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ይጠናከራል ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ዛሬ በድሬዳዋ የተጀመረው ድጋፋዊ የሥራ ጉብኝት ለ10 ቀናት የሚቆይ ነው።

በእዚህም በድሬዳዋ ዘርፉን የሚመራው ቢሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡትን የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች እንዴት እየፈጸመ እንደሆነ ይገመግማል፤ ውጤታማ እንዲሆኑም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ዜጎች በስልጠናና በክህሎት ታግዘው ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገበትን ሂደትና በየመስኩ ለነዋሪዎች የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን ቡድኑ እንደሚመለከት ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው እንዳሉት፤ በድሬዳዋ የሚስተዋለውን የሥራ አጥነት ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ ነው።

በድሬዳዋ ወጣቶችን ዕውቀት በማስታጠቅ የሙያ ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ሥራ በክህሎት እንዲመራ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ቡድኑ እያደረገ ያለው የሥራ ጉብኝት እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥራ በዘርፉ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረምና ጠንካራ ውጤታማ ተቋማትን በመገንባት የተሻለ ሥራ ለመስራት ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

የሚኒስቴሩ የባለሙያዎች ቡድን በሶማሌ ክልል አንዳንድ ከተሞችም በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን ቀደም ብሎ መመልከቱ ታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *