በፓሪስ ኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ የላቀ ውጤት እንድታስመዘግብ ዝግጅት እየተደረገ ነው::

Spread the love

በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው ኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ የላቀ ውጤት እንድታስመዘግብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በደሴ ከተማ የኦሎምፒክ ችቦ ማብራትና ቅብብሎሽ መርሃ-ግብር አካሂዷል፡፡

እንደኮሚቴው አገላለጽ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ውድድር በመጪው ሐምሌ ወር እንደሚካሄድም ታወቋል።

በውድድሩ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘገብ ከወዲሁ የቅደመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም በውጭና በሀገር ቤት ህብረተሰቡን የማነቃቃትና ግንዛቤ የመፍጠር፣ ገቢ የማሰባሰብ፣ ስፖርተኞችን የመመልመል፣ በክልሎች የችቦ ቅብብሎሽና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ስፖርት ለዘላቂ ሰላምና አብሮነትም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በስፖርት መተሳሰርና የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ማጠናከር እንዳለበትም ተመላክተዋል፡፡

በክልሎች መካከል የችቦ ቅብብሎሽ እየተካሄደ መሆኑ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከሩ ባለፈ ስፖርቱን ለማነቃቃትና ብቁ ተወዳዳሪ ለመፍጠር እያገዘ እንደሆነም ተገልጿል።

አማራ ክልል ከኦሮሚያ ክልል የተቀበሉትን የኦሎምፒክ ችቦ ዛሬ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስረክበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ እንዳሉት፤ በፓሪስ ለሚካሄደው ኦሎምፒክ የሚሳተፉ ብቁ ስፖርተኞችን ለማብቃት በቅንጅት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የኦሎምፒክ ችቦውን ከአማራ ክልል መረከባቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በማዘዋወር ዘርፉን ለማነቃቃትና የህብረተሰቡን አንድነት ለማጠናከር እንሰራለን ብለዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲና የደሴ ከተማ አመራር አባላትና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *