



በሼይ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ታደሰ ኒሳብ የተመራው የሀይማኖት አባቶች፣ የቀበሌ ተወካዮች፣ የነጋዴ ማህብረሰቦች፣ የሞዴል አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት ህንፃ እና የባታ ካሹ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ሂደትን ጉብኝት አድርገዋል።
ድልድዩ በህብረተሰብ ተሳትፎ በ25 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ መሆኑን ያብራሩት የሼይ ቤንች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ኒሳብ ስራው ሲጀመር በጀት ኑሮ ሳይሆን ህብረተሰቡ በገባው ቃልና ብርታት መሆኑን ገልጸዋል።
ድልድዩ ባለመሠራቱ የብዙ ሰው ህይወትና ንብረት እየጠፋ መቆየቱን አብራርተው ይህንኑን በይቻላል መንፈስ የተጀመረ መሆኑን አብራተዋል።
ግንባታውን በጋራ ተደጋግፈን ወደ ፍፃሜ ማድረስ አለብን ብለው ሁሉም ባለው አቅም በተለይ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በሀሳብ ፣ እንዲሁም በሌሎችም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ድልድዩ ሶስት ምሶሶ እና 30 ሜትር ርዝመትና 10 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው ያስረዱት በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን በሚዛን አማን ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አሸናፊ ወልዴ ግንባታው ወደ 55% መድረሱን ገልጸዋል።
የግንባታ ስራ ሲጀመር ብዙ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም በተቋራጩ ብርታትና በህበረተሰቡ ትብብር የሚታይ፣ ተስፋ ሰጪና አበረታች ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቦታው ለግንባታ ስራ አስቸጋሪ በመሆኑ እስካሁን ብቻ ወደ 200 ባጆ ደንጋይ ወስደዋል አሁንም አሁንም የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ጨረታውን አሸንፈው ግንባታውን እያከናወነ ያለው ተቋራጭ ይብራህ ገብረትንሳኤ ህብረተሰቡ ከገንዘቡ በተጨማሪ በጉልበቱና በሞራል እያበረታታ ያለውን ሁኔታን አመስግኗል።
ለድልድዩ ግንባታ የሲዝ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ፣የመስከረም ፍሬ፣ ሲሲ እና ማዝ ቀበሌ ህብረሰብ ክፍሎችና ሌሎችም ከገንዘብ በተጨማሪ በግንባታው ቦታ በመገኘት በጉልበት መደገፋቸውን የዘገበው የወረዳው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።
