




የኮንታ ዞን አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ተካሂዷል።
የአፈፃፀም ግምገማው በአስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና መሠረተ-ልማት ዘርፎች በመከፋፈል ነው የተገመገመው
በአፈፃፀም ግምገማው ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የተጣለባቸውን ተልዕኮ ለመወጣት ዕቅዳቸውንና አፈፃፀማቸውን እየፈተሹ ለውጤታማነት መትጋት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የህብረተሰቡን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ከማስጠበቅ ጀምሮ ፍትሃዊና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ በመግለፅ በቀሪ ወራት የታቀዱ ተግባራትን በሙሉ አቅም ተፈፃሚ ለማድረግ ሁሉ ዐቀፍ ርብርብ ማድረግና ለቀጣይ ዕቅድ መዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዞን ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሀብት ልማት መዋቅር የሰው ኃይሉን በመከታተልና በማስፈፀም ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን እርካታ ከፍ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው ተቋማት የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎት ለማርካት የተጀማመሩ መሠረተ ልማት ስራዎችን ማጠናከርና የህብረተሰብ ተሳትፎ በማሳደግ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የከተሞችን መሠረተ-ልማቶችን ማሟላትና ግንባታዎችን መከታተል ብሎም ተግባራትን በፓርቲ መርህ ተመስርቶ በየዘርፉ በተፈፀሙ ተግባራት የታዩ ጉድለቶችን መቅረፍና ጥንካሬዎችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ድህነት ቀናሽ በሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚታዩ መልካም ጅምሮች በበለጠ እንዲጠናከሩ የተገለፀ ሲሆን በተለይም በዞኑ በትምህርት፣ በመንገድ መሠረተ ልማት ፣በግብርናና በሌሎችም ያለውን ውጤት ማስቀጠል እንደሚገባ ተነግሯል።
የመምሪያዎች ኃላፊዎች ባቀረቡት 9 ወራት የአፈፃፀም ሪፖርት ወቅት በየዘርፉ የታዩ ማነቆዎችን ለመቅረፍ ቅንጅታዊ ስራዎች ማጠናከርና የህዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየፈቱ እየሄዱ እንደሚገኙ የጠቆሙ ሲሆን ከመዋቅሮች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ ስራዎችን ድጋፍና ክትትል ማሻሻል እንደሚገባ አንስተዋል።
በዞኑ ያለውን የኔትወርክና የመብራት ተደራሽነት ጥራት ችግሮች መቅረፍ፣ ገበያ ማረጋጋት ስራዎች፣ ኢንቨስትመንት አማራጮችንና ሌሎች ችግሮች በልዩ ትኩረት ሊሰሩ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል ሲል የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።
