




ከኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከክልሉ ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ መስሪያ ቤቶች እና የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቤንች ሸኮ ዞን የሚገኘውን የበበቃ ቡና ልማት፣ የቻንቹ ሙዝ ክላስተርን ጨምሮ ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በሚድሮክ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር በኢትዮ አግሪ-ሴፍት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የበበቃ ኮፊስቴት ከ2 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚና ከ10 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተገልጿል።
ኩባንያው በዓመት ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የታጠበ ቡና ለውጭ ገበያ እንደሚያቅርብ ተናግረዋል።
ኩባንያው ሰፊ መሬትና የሰው ሀይል በመያዝ የአከባቢውን ስነምህዳር በጠበቀ መልኩ የቡና ልማት ስራ እያከናወነ ጥራት ያለው ቡና ለአለም ገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት ስራ አስኪያጁ ምርትና ምርታማነት ላይ የሰው ሀይል የሚኖረው የላቀ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሠራተኞች በሰራተኛ ማህበር ተደራጅተው መብትና ጥቅማቸውን እያስጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በድርጅቱ የሸክላ ማምረቻ ፋብሪካ የተጎበኘ ሲሆን ፋብሪካው በቀን እስከ 10 ሺህ ሸክላ በማምረት ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ በገበታ ለትውልድ የዴንቢ ሰው ሰራሽ ሎጂ ግንባታ እያካሄደ ይገኛል ተብሏል።
በድርጅቱ ጥራት ያላቸው የሸክላ ምርቶች ለገበያ እያቀረበ ቢሆንም ፋብሪካውን ከማዘመን አኳያ የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸው ተገልጿል።
በኢፌዲሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት ፋብሪካው ከሚሰጠው ጠቀሜታና ከሚፈጥረው የስራ እድል አኳያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የማምረት አቅሙን ማሳደግ ይኖርበታል ብለዋል።
ሸክላ ከባህር ዛፍና ጭቃ ቤት የበለጠ ተመራጭና የቤትን ጥንካሬና ውበት የሚጨምር መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው በዘርፉ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀትና በማሰልጠን ወደ ስራ ማስገባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኩባንያው ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች መብቶቻቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንዲሁም ምርታማነትን ለማሳደግ በማህበር ተደራጅተው ውይይት በማድረግ መብትና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበት አሰራር ሊጠናከር ይገባል ተብሏል።
የተቋቋመው የሠራተኞች ነፃ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የመብራትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እየተመቻቸላቸው ቢሆንም ከደመወዝ አኳያ በሂደት መታየት ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የድርጅቱ ሰራተኞች ገልጸዋል።
ሌላው በደቡብ ቤንች ወረዳ በጃንቹ ክላስተር በ435 ሄክታር እየለማ የሚገኘው የሙዝ ክላስተር የተጎበኘ ሲሆን በክላስተሩ የህብረት ስራ ማህበራትና በማህበር የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ መሆናቸው ተጠቅሷል።
በቀን ከ10 እስከ 15 መኪና ሙዝ የሚጫንበትና 694 አርሶ አደሮች በክላስተር ያለሙት የሙዝ እርሻ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ምርቱን ለማጓጓዝ የመንገድ ውስንነት መኖሩ ተጠቅሷል።
በገበታ ለትውልድ የዴንቢ ሰውሰራሽ ግድብና ፏፏቴ ሎጂ ግንባታም በልዑካኑ ተጎብኝቷል።
