



የክልሉ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ የክልሉን የቪዲዮ ኮንፈራንስ አገልግሎት ይፋዊ ማስጀመሪያ ፕሮግራም አካሄዷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ዳንኤል የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት መጀመር ለክልሉ መንግሥታዊ አገልግሎት ውጤታማነት ፋይዳው የላቀ ይሆናል ብለዋል።
የቪዲዮ ኮንፈንስ አገልግሎቱ የመረጃ ልውውጥ ሂደትን የሚያቀላጥፍ ብሎም ጊዜ እና ሀብትን የሚቆጥብ ተመራጪ ቴክኖሎጂ መሆኑንም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል ።
ስለሆነም ለክልላችን የብዘሃ ማዕከላት መንግስታዊ ሥራዎች መሳለጥ ቴክኖሎጂው የተሻለ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ በተገቢው ልንጠቀም ይገባልም ብለዋል ወይዘሮ ቤተልሔም።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ በክልላችን አገልግሎቱ የዘገየው የኢኮቴ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ሲሆን አሁን ላይ የፌዴራል ብሔራዊ ዳታ ማዕከልን በመጠቀም አገልግሎቱን ለማስጀመር ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይ የክልሉን መረጃ ማዕከል ለመገንባትና ሌሎች አማራጮችን በዘላቂነት ለመጠቀም ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ምክትል አፌ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሐይ ዳርጫ እንዳሉት ቴክኖሎጂ ወደ ስራ መግባቱ በጎ ጅምር ነው ብለዋል።
በክልል ደረጃ የሚከናወኑ የውይይት መድረኮችን በዚሁ ቴክኖሎጂ ታግዘን የምናስፈጽም ከሆነ ውስን የሆነውን ሀብት እና ውድ ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም እንችላለን ብለዋል።
እንደ ምክትል አፌ ጉባኤዋ ገለጻ ቴክኖሎጂው ከሚያበረክተው ፋይዳ አንጻር በክልላችን የብዝሃ ማዕከላት የሚገኙ ቢሮዎች እና ተቋማት አገልግሎቱን በተገቢው ሊጠቀሙ ይገባል።
በማስጀመሪያው ወቅት ከቦንጋ እና ታርጫ ማዕከላት በቴክኖሎጂው የተሳተፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋፋትና ደረጃውን ለማሳደግ ከቢሮው ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል ።
በመድረኩ በየማዕከላት የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎቸና ባለሙያዎች ካሉበት ሆነው ውይይቱን የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይም ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው አፈፃፀማቸውን እንደሚገመግሙ ተነግሯል።
