












ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየዉ የየደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2016 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ አካላት የማጠቃለያ የተግባር አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የበጀት ዓመቱን የተግባር አፈጻጸም በጥልቀት ገምግሞ በቀጣይ የትኩረት መስኮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በጤናው ዘርፍ በክልሉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጤና ቢሮ የተጀማመሩ የንቅናቄ ተግባራት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳሰቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) የመድሃኒት ዕጥረትን ለመፍታት ጠንከር ያለ ክትትል መደረግ እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በመንግሥት የጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦትና አስተዳደር ስራን የጤና ቢሮ ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው ከወትሮው በተለየ ስልት ቀይሶ መምራት እንዳለበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ገልጸዋል።
በትምህርት ዘርፍ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል እና የፈተና አስተዳደር ስርዓት ለማሳለጥ የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የጠቆሙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምህርት ጥራትን በተገቢው ለማሻሻል የመምህራን አቅም ግንባታ ስራዎችን የማጠናከር እንዲሁም በክልሉ ተጀምሮ ውጤታማ የኾነውን የትምህርት ቤት የደረጃ ማሻሻያና የትምህርት ግብዓት ማሟላት ተግበር በቀጣይ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በክህሎትና ቴክንክ ሙያ ስራዎች የተማሪዎች ቅበላና የኢንዲስትሪ ኤክስቴንሽን ስራዎች እንዲጠናከሩ አሳስበዋል ።
በመልካም አስተዳደርና የህግ ጉዳዮች በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ውጤት በዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እንዳለው ያመላከተ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ አጠቃላይ ክልላዊ ሠላምን ለማስፈን የፀጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው በሰራው ስራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና የኮንትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ተግባራትን የታችኛውን መዋቅር የፀጥታ መዋቅር በማቀናጀት መከላከል እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ውድ የሆነውን የሰው ህይወት እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ አደጋ ከመከላከል ረገድ የሚታየውን የስነምግባር ችግር ማረም እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
የመንግሥት ሠራተኞች የትምህርት መረጃ ማጥራት፣ ውጤታማነት መለካትና በሂደቱ የሚስተዋሉ ጉዳዮች መፍታት የሚችል የአሰራር ስረዓት መዘርጋት የቀጣዩ ትኩረት መስክ እንዲሆን ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች በመከታተል በህግ አግባብ ማስጠየቅ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት በመንግሥትና ህዝብ መካከል ድልድይ በመሆን ወቅታዊና ተዓማኒነት ያላቸው መልዕክቶች ተደራሽ እያደረገ ያለው ተግባር መጠናከር እንዳለበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ለብሮድካስት የሚመረቱ ዜናዎች በጥራትና ብዛት መጨመር እንዳለበትም አንስተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ካለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም አኳያ የተሻሉ እንደሆነ በመግልጽ በድክመት የተነሱ ጉዳዮች ተቋማት ለቅመው በመውስድ በአዲሱ በጀት ዓመት የእቅድ አካል በማድረግ በ2017 በጀት አመት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጧል።
የመድረኩ ተሳታፊ የየተቋማቱ አመራሮች በበኩላቸው በድክመት የተነሱት ጉዳዮች ፈጥኖ በማረም በቀጣይ በጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
