የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነው ደም ልገሳ ተግባር በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እየተከናወነ ነዉ።

Spread the love

የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ደም በመለገስ ሁሉም መሳተፍ እንደሚገባውም ተጠይቋል።

የበጀት ዓመቱን ማጠቃለያ ግምገም በማድረግ ላይ የሚገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ደም በመለገስ ተሳትፈዋል ።

የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተመስገን ከበደ የሰው ልጅ ህይወት እየሰጠ በደም እጥረት ህይወቱን እንዳያጣ ደም በመለገስ ህይወቱን ማትረፍ ይኖርብናል ብለዋል።

ደም መለገስ ህይወትን የመታደግ ትልቅ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ ተመስገን ጠይቀዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ደም ከ3 ወራት በኋላ ከሰውነታችን በተለያየ መንገድ በቆሻሻ መልክ ይወገዳል ። ይህንን ደም ከ3 ወር አንዴ ደም በመለገስ የዜጎችን ህይወት መታደግ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል ።

በክልሉ በወሊድ፣በድንገተኛ አደጋና በወባ በሽታ ሳቢያ የሚከሰተውን የደም ዕጥረት በመከላከል ጤናማ የሆኑ ዜጎች በታርጫ የደም ባንክ ማዕከልና በቦንጋ የደም ባንክ ማዕከል በመገኘት ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት የደም ልገሳ በቀጣይም በሁሉም አካባቢዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የዜጎችን ህይወት መታደግ ይኖርብናል ብለዋል አቶ ኢብራሂም ።

የክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ዳንኤል ደም መለገስ ወገናዊነትን የሚያንጸባርቅ የህሊና እርካታን የሚሰጥ በጎ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

ደም መለገስ ህይወትን የማትረፍ ጉዳይ በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ደም ለሚፈሳቸው ወገኖች ደም በመለገስ ህይወታቸውን መታደግ ይኖርብናል ብለዋል።

ደም በመለገስ የተሳተፉ አመራሮች ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ማጠናከር ይገባልም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የቦንጋ ደም ባንክ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ገሸሬ በክረምቱ መርሃ ግብር ከ2000 በላይ የደም ዩኒቶችን ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመርሃ ግብሩ አንድ አካል የሆነው ይኸው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የደም ልገሳ ፕሮግራም በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንዲሰራ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

ደም መለገስ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ያብራሩት አቶ ፍቃዱ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ካንሰር፣የልብ ህመምና ግፊት የመሳሰሉ በሽታዎችን 50 ከመቶ መከላከል እንደሚያስችልም ተናግረዋል ።

ደም በመለገስ የእናቶችንና የህጻናትን እንዲሁም በተለያዩ አደጋዎች ደም የሚፈሳቸውን ወገኖች ከመታደግም በላይ ደም ለጋሹ በህይወት የመኖር ዕድሜውን የሚያራዝም መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *