

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ከ 85 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን የሲቲስካን ማሽን አስገብቷል።
የሲቲስካን ማሽኑ ወደ ሆስፒታሉ መምጣት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ይቀርፋል።
ሆስፒታሉ ከ 2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን የማሽኑ መገዛት ካለው የተገልጋይ ቁጥር አንጻር አስፈላጊ ነው ተብሏል።
የዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እርቅይሁን ጳውሎስ እንደገለጹት የሲቲስካን ማሽኑ መገዛት 27 በመቶ የሚሆነውን የሪፈራል መጠን ይቀንሳል ብለዋል።
ሆስፒታሉ በቀጣይም የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ህብረተሰቡን ለማገልገል ይሰራል ያሉት ዶ/ር እርቅይሁን የኦክስጅን ማምረቻ እና የደም ባንክን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማስጀመር ይሰራል ብለዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም ዩኒቨርሲቲው የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚጓዝበት መንገድ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
አሁንም ሊሰሩ የሚገባቸው ተግባራት እንዳሉ ከንቲባው ገልፀው ሁሌም የቅሬታ ምንጭ የሚሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዋቆ ገዳ እንደገለጹት ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ መፍታት ባይቻልም በሂደት ግን ለህብረተሰቡ ጥያቄ በተለይ በጤናው ዘርፍ ምላሽ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሲቲስካን ማሽኑ ያለውን ችግር ለመፍታት 85 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን ገልጸው ለሆስፒታሉ ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በሆስፒታሉ የሚነሱ ሌሎች ቅሬታዎችንም ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል ሚዛን ፋና ኤም 92.5
ዘግቧል።
