








በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት ስራዎቻችንን በተሳለጠና በተግባባ መልኩ ለማከናወን የአስተሰሰብና የተግባር አንድነትን በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የአሰባሳቢና ገዢ ትርክትን በሕዝብ ዘንድ በማስረጽ አብሮነት ለማጽናት የሚዲያ ባለሙያዎች አብነታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማረጋገጥና የብልፅግና ጉዞ ለማጽናት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡
የስልጠና መርሃ ግብሩ ‘’የብሔራዊ ትርክት ግንባታ ለኢትዮጵያ ልዕልና’’ በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ሲሆን ከጋምቤላ ክልል፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ፣ ሆሮጉድሩ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉባቦር፣ ቄለም ወለጋ፣ የጅማ ከተማና ዞን የተወከሉ 425 የሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡
የስልጠና መርሃ ግብሩ 5 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ብሔራዊ ትርክትን ለማስረጽ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡
