




የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኦየስ ግሎባል ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ግሎባል ሲቲዝን ፕላስ 2024 የተሰኘው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባዔው በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላምና ግጭት አፈታት እንዲሁም በሌሎች በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ዛሬና ነገ የሚካሄድ ይሆናል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፤ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የጤና ችግር፣ የምጣኔ ኃብት ድቀትና ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ እያስከተለ መሆኑን ዘርዝረዋል።
በመሆኑም ለዚህ ዓለም አቀፍ ችግር ዘላቂ መፍትሔ በመሻት የበለፀገችና ፍትሃዊነት የተረጋገጠባትን ዓለም ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የጋራ ጥረትና ትብብርን ይሻል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ነድፋ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባው ጉባዔም ለዚህ ውስብስብ ችግር የተለያዩ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚቀርቡበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚገጥሙ የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመቋቋም በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለያዩ የመረዳጃ መንገዶች መኖራቸውን የገለፁት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔ ሰዓዳ አብዱራህማን ናቸው።
የኦየስ ግሎባል ፋውንዴሽን መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ከማል አብደላ፤ ከ30 በላይ ሀገራት ተሳታፊዎች የታደሙበት ጉባዔ በመሠረታዊ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ በማተኮር የሚመክር መሆኑን ተናግረዋል።
በጉባዔው የሚቀርቡ ምክረ-ሃሳቦች ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ተጨማሪ ግብዓት እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።
በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው ጉባዔው እየገጠሙ ላሉ ዓለም አቀፍ ችግሮች የመፍትሔ ምንጭ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
