እንደ ንብ ታታሪዋ እንስት ››

Spread the love


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በንብ ሀብት እምቅ አቅም እንዳለው ይታወቃል፡፡

የማርና ሰም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በክልሉ ከባለፉት ዓመታት ጀምሮ በንብ ሀብት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡

የተለያዩ የእንስሳት ልማት የቴክኖሎጂ/ጥንቅሮች ወይም ፓኬጆች ተዘጋጅተው በየአካባቢው እንደ አመችነታቸው እዲተገበሩ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

በቀበሌ ደረጃ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ የልማት ጣቢያ ሠራተኞችን በማሰማራት ለተጠቃሚ አናቢዎች ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ በማድረግ የአናቢው ዕውቀትና ክህሎትን በማዳበር የማይናቁ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በክልሉ ባሉ ዞኖች በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ፣ በሥርዓተ _ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ በንብ ማነብ የተሰማሩና ውጤታማ የሆኑ ሴት አናብዎች ምርጥ ተሞክሮ ተቀምሮ ለሌሎች መነሳሳትን እንዲፈጥር ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በክልሉ ባሉ ዞኖች በንብ ሀብት ልማት ዘርፍ የተሰማሩና ውጤታማ የሆኑ የሴቶችን ምርጥ ተሞክሮ በመቀመር ለሎች እንድማሩበት የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በዚህም ረገድ ሞዴል ከሆኑት ሴቶች መካከል በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ኡዋ ቀበሌ ካፈሯቸው ሞዴል ንብ አናቢዎች መካከል ወ/ሮ አስናቀች መኮንን ተጠቃሽ ናቸው ፡፡

ወ/ሮ አስናቀች ጨፈቃ ቀፎዎችን በመነሻነት ይዘው በ2010 ዓ/ም ንብ በማንባት 180 ኪሎ ግራም ማር በማግኘት ስራቸውን መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡

ቀፎ በመስቀል በሚያገኙት የማር ምርት ወደ ገንዘብ በመቀየር ልጆቻቸውን እስከ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል ፡፡

ከዚህም ባለፈ 28 ቅጠል ቆርቆሮ ቤት በመስራትም ኑሯቸውን እየመሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል ፡፡

ወ/ሮ አስናቀች በጠቅላላው ወደ 64 የሚጠጉ ቀፎዎች በ4 ጋጣዎች እንዳላቸውና በ58 ቀፎዎች ንብ በማስገባት ከፍተኛ ማር እያገኙ እንደሚገኙና ይህንንም ስራ አስፋፍተው ለመስራት ዕቅድ እንዳላቸውም አስረድተዋል ፡፡

ዘንድሮ 1 ሺህ 400 ኪሎግራም ማር ማግኘታቸውና ገና ያልተመዘነ ማር በእጃቸው እንደሚገኝም አብራርተዋል ፡፡

ለስራቸው ውጤታማነት ባለቤታቸው ከጎናቸው መሆኑንና የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉት ድጋፍም ለዚህ አብቅቶኛል ሲሉ ይናገራሉ ፡፡

ባላቸው የእርሻ ማሳ ይዞታቸው አንድ ሄክታር ኮረሪማ ፣ 20 ኪሎግራም ጥምዝ በማምረት ሽጠው መጠቀም እንደቻሉ ወ/ሮ አስናቀች ታታሪነታቸውን ገልጸዋል ፡፡

ወ/ሮ አስናቀች በመንደራቸው ሌሎች ሴቶችን ወደ ንብ ማንባት ስራ እንዲሰማሩ ጥረት ቢያደርጉም ጥቂቶች ብቻ የእሳቸውን ፈለግ ለመከተል መነሳሳት እንዳላቸው ቢብራሩም አሁንም ሴቶችን ወደ ለውጥ ለማስገባት ጥረታቸውን እንደማያቋርጡ ተናግረዋል ፡፡

ያመረቱትንየማር ምርት በተሻለ ገበያ ሽጠው ለመጠቀም እንዲያስችላቸውም የመንገድ መሰረተ ልማት በአካባቢያቸው እንዲሰራላቸውም ጠይቀዋል ፡፡

በክልሉ በሁሉም ዞኖች በግብርናው ልማት መስክ የሴቶችን ውጤታማነት ላመረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል ፡፡ በተከናወነም ስራዎች ንብ በማነብ ስራ ውጤታማ የሆኑትን ሴቶች ተሞክሮ በመቀመር 49 ሴቶች ተለይተው በክልል ማዕከል እንዲበረታቱ የንብ ማነቢያ ቁሳቁስ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ፡፡ ይህ የተበረከተላቸው ቁሳቁስ ይበልጥ ለስራ እንደሚያነሳሳቸውም ወ/ሮ አስናቀች ተናግረዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *